Fana: At a Speed of Life!

በሆሳዕና ከተማ የሀገር መከላከያ ሠራዊትን የሚቀላቀሉ ዘማቾች በክብር ተሸኙ

 

አዲስ አበባ፣ ህዳር 5 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀገሪቱን ከአሸባሪው የሕወሐት ሴራና የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት በጋራ ህዝባዊ ተሳትፎ በመመከት የቀደመ የጀግንነት ታሪኳን መድገም እንደሚገባ ተገለፀ።

በሀዲያ ዞን ሆሳዕና ከተማ የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ለሚቀላቀሉ አመራሮች፣ ተመላሽ የሠራዊት አባላትና ተጠባባቂ ኃይሎች የሽኝት መርኃ-ግብር ተካሄዷል።

የሀዲያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማቴዎስ ሎምበሶ አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ባለፉት 27 ዓመታት ሀገሪቱን በብሔር፣ በሃይማኖትና ጎሳ ፖለቲካ ሲለያይ የቆየ መሰሪ ቡድን መሆኑን ጠቁመው ይህ ጽንፈኛ ቡድን በለውጡ መንግስት ያጣውን ስልጣን ለመመለስ ብርቱ ትግል እያደረገ ይገኛል ብለዋል። ይሁን እንጂ በዜጓቿ የተባበረ ክንድ ሴራው እንደሚከሽፍ ጥርጥር የለኝም ነው ያሉት።

የትግሉን ጊዜ በአጭሩ በመቋጨት ሀገሪቱ ከጦርነት ተላቃ ፊቷን ወደ ልማት እንድታዞር የሁልጊዜ የትግሉ አጋር የሆነው የዞኑ ህዝብ መከላከያ ሠራዊትን ለሚቀላቀሉ አመራሮች፣ ተመላሽ ሠራዊት አባላትና ተጠባባቂ ኃይሎች ደማቅ የአሸኛኘት መርኃ-ግብር መካሄዱን አቶ ማቴዎስ ገልፀዋል።

ዞኑ የህልውና ዘማቾችን ከመሸኘት ባለፈ ከ750 በላይ ሰንጋዎችን፣ 300 ሙክቶችንና 100 ኩንታል የተለያዩ የስንቅ ዓይነቶችን አብሮ እንደላከ የገለፁት አስተዳዳሪው ሀገሪቱን ከአሸባሪው የሕወሐት ሴራና የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት በጋራ ህዝባዊ ተሳትፎ በመመከት የቀደመ የጀግንነት ታሪኳን መድገም የሁሉም ኃላፊነት ነው ብለዋል።

የሀዲያ ዞን ሠላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ አረጋ ማዴቦ በበኩላቸው የዞኑ ህዝብ ለበርካታ ጊዜያት በተለያዩ መንገዶች ለሀገር መከላከያ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰው በቀጣይም የአሸባሪው ግብዓተ መሬት እስኪፈፀም ከቁሳዊ ድጋፍ እስከ ግምባር ዘመቻ አጋርነቱን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በሽኝት መርኃግብሩ የተገኙት የደቡብ ክልል የሥራ ዕድል ፈጠራና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ቢረጋ ብርሃኑ መኖር የሚቻለው ሀገር ስትኖር እንደሆነ በመጠቆም የቀደምት ጀግኖች ሀገር ትሩፋት የሆነው የዞኑ ህዝብ ላሳየው ጥልቅ የሀገር ፍቅር ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የሀገር መከላከያን እንዲቀላቀሉ ሽኝት ከተደረገላቸው የህልውና ዘማቾች መካከል መቶ አለቃ ሰይፉ ጉልላትና አቶ ሄኖክ ሉሌ ከቀደምት አባቶቻችን የወረስናት የሽንፈት ታሪክ የሌላት ሀገር በጠላት ስትወረር ዝም ብለን አናይም ነው ያሉት።

አስተያየት ሰጪዎቹ አክለውም ለሉዓላዊቷ እናት ሀገር ህልውና እስከግምባር በመዝመት የዜግነት ግዴታቸውን ለመወጣት ዕድል በማግኘታቸው ደስተኞች መሆናቸውን ገልፀዋል።

ምንጭ:-ደሬቴድ

አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.