በዶ/ር ኢ/ር ስለሺ የተመራ ልኡክ ከግብፅና ሱዳን ጋር የተደረገውን የህግ ማዕቀፍ ድርድር ውጤት በዋሽንግተን ዲሲ መገምገም ጀመረ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 3፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ የተመራው የኢትዮጵያ ልኡክ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ከግብፅ እና ሱዳን ልዑካን ጋር የተደረገውን የህግ ማዕቀፍ ድርድር ውጤት በዋሽንግተን ዲሲ መገምገም ጀመረ።
ሚኒስትሩ የህግ ማዕቀፍ ድርድር ውጤቱን ለመመልከት በትናንትናው እለት አሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ መግባታቸውን በትዊተር ገፃቸው አስታውቀዋል።
በዕለቱም በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ከግብፅ እና ሱዳን ልዑካን ጋር የተደረገውን የህግ ማዕቀፍ ድርድር ውጤትን የኢትዮጵያ ልዑክ ገምግሟል።
ቡድኑ በበርካታ ጉዳዮች ላይ ምክክር ያደረገ ቢሆንም፥ ስምምነት ላይ ሊያደርስ የሚችል ሰነድ በጋራ ማዘጋጀት አለመቻሉ ታይቷል።
የህግ ማዕቀፍ ድርድሩ በዛሬው እለትም የሚቀጥል መሆኑን ነው ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ያስታወቁት።
ከዚህ ቀደም በተደረገው ውይይት ላይ በተያዘው ቀጠሮ መሰረት የኢትዮጵያ፣ የግብፅ እና የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እና የውሃ ሚኒስትሮች በነገው እለት በዋሽነግተን ዲሲ ተገናኝተው የህግ ማዕቀፍ ድርድር ውጤት ላይ የሚመክሩ ይሆናል።
የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስትር እና የአለም ባንክ ተወካዮች በነገው የውይይት መድረክ ላይ እንደሚገኙም ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ልኡክ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ በሚደረጉ ድርድሮች ላይ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ጠንክሮ እንደሚሰራም ገልፀዋል።