ጠ/ሚ ዐቢይ ከተለያዩ ሃገራት መሪዎች ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ ፣ የካቲት 2፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከተለያዩ ሃገራት መሪዎች ጋር ተወያዩ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከደቡብ ሱዳኑ ፕሬዚዳንት ሳልቫኪር ማያርዲት ጋር በሃገሪቱ ዘለቂ ሰላምን ማስፈን በሚቻልበት አግባብ ላይ መወያየታቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።
በውይይታቸውም በሃገሪቱ የሽግግር መንግስት ምስረታ ሂደት ላይ የተደረሰው ስምምነት እንዲተገበር በጋራ ለመስራት መስማማታቸውን አስረድተዋል።
ከዚህ ባለፈም ከደቡብ ሱዳን በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎች ተፈናቅለው በኢትዮጵያ መጠለላቸውን በመጥቀስ፥ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች በኢትዮጵያ ላይ በሚያሳርፈው ተፅዕኖ ዙሪያም መክረዋል።
ከዚህ አንጻርም የደቡብ ሱዳን ሰላም ለኢትዮጵያና ለአካባቢው ሃገራት ቁልፍ መሆኑንም በዚህ ወቅት ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ከጁቡቲው ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማር ጊሌህ ጋር ባደረጉት ውይይት ደግሞ በመሰረተ ልማት ማሻሻያ በተለይም ከወደብ አገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ምክክር አድርገዋል።
ከዚህ ባለፈም የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎትን ቀልጣፋ ማድረግ በሚቻልበት አግባብ እንዲሁም በምጣኔ ሃብታዊ ውህደት ዙሪያም ተወያይተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጊኒው ፕሬዚዳንት አልፋ ኮንዴ ጋርም በአህጉራዊ እና ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ መክረዋል።
በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአልጄሪያው ፕሬዚዳንት አብዱልመጂድ ቲቦን ጋር የምስራቅ አፍሪካን እና የሳህል ቀጠናን ትስስር ማጠናከር በሚቻልበት አግባብ ላይ ምክክር አድርገዋል።
መሪዎቹ በኢትዮጵያ እና በአልጄሪያ መካከል ያለው የመደመር ግንኙነት ለሁለቱም ሀገራት የሚጠቅም ትብብርን የማስገኘት አቅም እንዳለውም አንስተዋል።
በስላባት ማናዬ
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision