በትግራይ ክልል የዘር ማጥፋት ተፈጽሟል በሚል የቀረበው ውንጅላ መሰረተ ቢስ ነው – ዓለም አቀፍ ሪፖርት
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽሟል በሚል የቀረበው ውንጀላ ሃሰተኛ መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽህፈት ቤት የጋራ ሪፖርት አመላከተ።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽህፈት ቤት የትግራይ ክልል የሰብዓዊ መብት አያያዝን አስመልክቶ በጋራ ያካሄዱትን የምርመራ ውጤት ሪፖርት ይፋ አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የጋራ የምርመራ ሪፖርቱን በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው ተቋማቱ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል እየተካሄደ ካለው ግጭት ጋር ተያይዞ ባለው የሰብዓዊ መብት አያያዝ ዙሪያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ላደረጉት ምርመራ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ምንም እንኳ በሪፖርቱ አንዳንድ አቅጣጫዎች ላይ መሰረታዊ ልዩነቶች ቢኖረንም ሪፖርቱ ጠቃሚ ሰነድ በመሆኑ ዕውቅና የሚሰጠውና ተቀባይነትም ያለው ነው ብለዋል።
አክለውም ሪፖርቱ ተጎጂዎችን ለመታደግ፥ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የመከላከል እርምጃዎችን በመውሰድ ረገድ መንግስት እያካሄደ ያለውን ጥረት ለማካካስ እንደሚጠቅም አስረድተዋል።
ከዚህ ባለፈም የምርመራ ሪፖርቱ ግጭቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ኢትዮጵያውያን የደረሰባቸውን ሰቆቃ እና ጉዳት የያዘ መሆኑን አንስተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው በመንግስት ላይ የቀረቡ መሰረተ ቢስ እና መሰሪ ውንጀላዎችን ሪፖርቱ ውድቅ አለማድረጉ እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል።
በተለይም ለትግራይ ክልል ነዋሪዎች እርዳታ እንዳይደርስ እና ረሃብን እንደ ጦር መሳሪያ ሆን ብሎ ተጠቅሞበታል” ለሚለው ውንጀላ የቡድኑ ሪፖርት ምንም አይነት ማስረጃ አላገኘሁም ሲል መጥቀሱን አንስተዋል።
“ይህን መሰሉ ውንጀላ ሃሰት እንደነበር እናውቃለን”ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ጠላቶቻችን ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ለማሳሳት ያለ እረፍት እንደሚሰሩ ጠቁመዋል።
በሚያሳዝን ሁኔታ ግን በርካታ ሃገራት ከኢትዮጵያ ጋር የነበራቸውን የረጅም ጊዜ ግንኙነት በመተው እርምጃ ለመውሰድ እነዚህን ሃሰተኛ መረጃዎችን መጠቀማቸውን ጠቅሰዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሪፖርቱ በህዳር ወር መጀመሪያ ሳምሪ ተብሎ የሚጠራ የትግራይ ወጣቶች ቡድን በማይካድራ የአማራ ንጹሃን ዜጎችን የጨፈጨፉበትን ሁኔታ ማካተቱንም አንስተዋል።
የጋራ የምርመራ ሪፖርቱ “የትግራይ ልዩ ሃይል እና ሚሊሻ” ተብለው የተገለጹት የአሸባሪው ቡድን ታጣቂዎች፥በቁጥጥራቸው ስር የዋሉ የመከላከያ ሰራዊት አባላትን እንዲሁም ሌሎች ንፁሃንን ብሔርን መሰረት ባደረገ መልኩ ጥቃት እንደፈጸሙባቸው አረጋግጧል።
ይህ የጋራ ሪፖርትም ያልተገለጹ የሽብር ቡድኑን በርካታ ጥፋቶች የሚያሳይና መንግስት ሲያቀርባቸው የቆዩ መረጃዎችን ተዓማኒነት የሚያሳድግ ይሆናል ተብሏል።
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!