በኦሮሚያ ክልል 19 ዘመናዊ የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ ጥር 29፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኦሮሚያ ክልል በዘንድሮው ዓመት ብቻ በክልሉ የ19 ትላልቅ የዘመናዊ መስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ መጀመራቸውን አስታወቀ።
ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት የክልሉ ገጠር ክላስተር አስተባባሪ ዶክተር ግርማ አመንቴ 19ኙ ፕሮጀክቶች በፌደራል እና በክልሉ መንግስት በጀት እንደሚገነቡ ገልጸዋል።
ከእነዚህ ፕሮጀክቶች መካከል 7ቱ በፌደራል መንግስት ወጪ ሲገነቡ 12ቱ ደግሞ በክልሉ መንግስት ይገነባሉ ነው የተባለው።
ለፕሮጀክቶቹ የፌደራል መንግስት ከ15 ቢሊየን ብር በላይ ፈሰስ የሚያደርግ ሲሆን፥ ፕሮጀክቶቹ ሲጠናቀቁ ከ120 ሺህ በላይ ማሳ የማልማት አቅም እንዳላቸው ተጠቁሟል።
በግንባታ ላይ ካሉት የመስኖ ፕሮጀክቶች በተጨማሪ ግንባታቸው ተጠናቆ ለአገልግሎት የበቁም እንዳሉም ሃላፊው አንስተዋል።
አርጆ ዴዴሳን እና ጉዳር የመስኖ ፕሮጀክቶችን የሚያካትተው ይህ በፌደራል ደረጃ የሚገነባው ፕሮጀክት ከ57 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ የሚያለማ ነው ተብሏል።
ዝናብ ወቅቱን ጠብቆ ያለመዝነብ እና በተለያዩ ጊዜያት የሚከሰቱ የድርቅ አደጋዎች፥ በርካቶችን ለርሃብ እና ችግር ሲዳርጉ ከእያዳንዱ አርሶ አደር ጉርስ ከፍ ባለ ደረጃም የሀገር ኢኮኖሚ ላይ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል።
ስለሆነም የግብርናውን ዘርፍ ምርታማነት በማሳደግ እስካሁን በቤተሰብ ደረጃ ማረጋገጥ ያልተቻለውን የምግብ ዋስትና ለማረጋጋጥ ደግሞ ዘርፉን በመስኖ ልማት ማገዝ መፍትሄ መሆኑን አንስተዋል።
ክትትል እና ድጋፉ መንግስት ማስጀመር ብቻ ሳይሆን ተከታትሎ የማስጨረስ ሀላፊነት እንዳለበት በሚያመላክት የሀላፊነት ደረጃ ይከናወናልም ብለዋል።
አርሶ አደሮችም ቢሆኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ በመስኖ ልማት ለመሳተፍ ፍላጎት እያሳዩ መሆኑ ተነግሯል።
በክልሉ ከ36 ሚሊየን ብር በላይ የፈጀው እና ከ400 ሄክታር መሬት በላይ የሚያለማው የወልመል መስኖ ፕሮጀክት እና የጨልጨልም ፕሮጀክት የክልሉ ሌላ የመስኖ ልማት ተስፋ ናቸው ተብሏል።
በአፈወርቅ አለሙ