Fana: At a Speed of Life!

ህብረተሰቡ የህወሃትን ጁንታ ቡድን ሰርጎ ገቦች በማጋለጥና አካባቢውን በንቃት በመጠበቅ ጠንካራ ደጀንነቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ህብረተሰቡ የህወሓትን ጁንታ ቡድን ሰርጎ ገቦችን በማጋለጥና አካባቢውን በንቃት በመጠበቅ ጠንካራ ደጀንነቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል መንግስት መልዕክት ማስተላለፉን የኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ባወጣው መግለጫ፥ አሸባሪው የህወሃት ጁንታ ቡድን ደሴ ከተማን ኢላማው አድርጎ ያቀዳቸው በርካታ የጥፋት ስራዎች እንደማይሳኩለትም ገልጿል።

አሸባሪው የህወሃት ጁንታ ቡድን በሁሉም ግንባሮች በጀግናው የመከላከያ ሰራዊታችን፣ በአማራ ልዩ ሃይልና ሚሊሻ እንዲሁም ለህልውናቸው በተሰለፉት የክልሉ ወጣቶች የሚደርስበት ከባድ ኪሳራ ሩቅ እንደማያስኬደው አብራርቷል።

ህብረተሰቡም የዚህን ሽብር ቡድን እኩይ አላማና እቅድ በመረዳት ሃገርን ለመበታተን አቅዶ የተነሳውን የጥፋት ሃይል ሴራ ማክሸፍ ይገባዋል ብሏል።

የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

አሸባሪው የህወሓት ጁንታ ቡድን ደሴ ከተማን ኢላማው አድርጎ የሚያቅዳቸው በርካታ የጥፋት ስራዎች መኖራቸው የሚታወቅ ነው።

በሁሉም ግንባሮች በጀግናው የመከላከያ ሰራዊታችን፣ በአማራ ልዩ ሃይልና ሚሊሻ እንዲሁም ለህልውናቸው በተሰለፉት የክልሉ ወጣቶች የሚደርስበት ከባድ ኪሳራ ሩቅ እንደማያስኬደው ግልጽ ሆኗል።

የደሴ ከተማ ላይ ያቀደው ጥፋትም ይህንኑ ሽንፈቱን በጥፋት ስራ ለመሸፈን ማቀዱን ያሳያል።

ህብረተሰቡም የዚህን ሽብር ቡድን እኩይ አላማና እቅድ በመረዳት ሃገርን ለመበታተን አቅዶ የተነሳውን የጥፋት ሃይል ሴራ ማክሸፍ ይገባዋል።

የሽንፈት ገፈትን እየቀመሰ የሚገኘው የሽብርተኛው ቡድን በደሴ ብዙ ሰራዊት ሊኖር ይችላል በሚል በተጨማሪም ፋኖ የከተማ የውጊያ ስልትን ለማካሄድ ሊዘጋጅ ይችላል የሚል ግምትን በማሳደር ሰርጎ ገቦችን በመጠቀም በከተማዋ የመብራት መስመሮችን ለማቋረጥ እና በደሴ የሚገኘው የፀጥታ ሃይል ላይ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫናን ለማሳደር ማቀዱን የሚያሳዩ መረጃዎች ወጥተዋል።

በከተማዋ የሚገኘው የመከላከያ ሰራዊትም ሆነ የክልሉ ልዩ ሃይልና ሚሊሻ ከመረጃ እንዲርቅ ማድረግንም በእቅዱ ይዟል።

ሃሰተኛ መረጃዎችንና ምስሎችን በስፋት በማሰራጨትም የሰራዊቱንና አጠቃላይ የፀጥታ ሃይሉን ሞራል ለማዳከም ያስችሉኛል በሚል የያዛቸው እቅዶች መኖራቸው ተደርሶበታል።

ይህ የጥፋት ቡድን ሃገርን ማሸበር ዋና አላማው መሆኑን የሚያሳይ ነው።

የአማራ ክልል ህዝብና መላው ኢትዮጵያውያን የሽብር ቡድኑ ህወሃት ያቀዳቸውን የማወናበጃና የህብረተሰቡን ኢኮኖሚና ማህበራዊ ተግባራት የማወክ እንቅስቃሴን ቀድሞ በመረዳት ሰርጎ ገቦችን በማጋለጥና አካባቢውን በንቃት በመጠበቅ እንደስካሁኑ ጠንካራ ደጀንነቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል መንግስት መልእክት ያስተላልፋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.