መውሊድን በእማማ ረህመት በሺር ቤት
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 8፣ 2014 (ኤፍ ቢሲ) የ80 አመት አዛውንቷ እማማ ረህመት የጎንደር ከተማ ነዋሪ ናቸው።
ለሀገራቸው ያላቸው ፍቅር ቀላል የሚባል አይደለም።
የሚተዳደሩት በልጆቻቸው እርዳታ ቢሆንም ሀገራቸው በትህነግ አሸባሪ ቡድን የገባችበትን ችግር ለማስወገድ ግንባር ለዘመተው ሰራዊት 1ሺህ እንጀራና 50 ኪሎ ሽሮ አዘጋጅተው ድጋፍ አድርገዋል።
እኛም ይህንን የመሰለ ስራ በዚህ የኑሮ ሁኔታና እድሜ መከወናቸውን ስንሰማ መውሊድን እያከበሩ እንድንጨዋወት እንግዳችን አደረግናቸው።
“ሀገር ያለሰው ምንም ናት” የሚሉት እማማ ረህመት የእናት አባቶቻቸውን የጀግንነት ታሪክ እያስታወሱ እኛም የዚህ ዘመን ትውልዶች ታሪክ ሰሪ ልንሆን ይገባል ይላሉ።
እርሳቸው መሳሪያ ታጥቀው ግንባር ድረስ መዝመት ባይችሉም ለዘማች የሰራዊት አባላት ግን የእናትነት ድጋፋቸውን አሳይተዋል።
ከእለት ቀለባቸው ቀንሰው ባጠራቀሟት ገንዘብ አንድ ሺህ እንጀራና አምሳ ኪሎ ሽሮ በማዘጋጀት ግንባር ድረስ ዘልቀው አስረክበዋል።
ዛሬ ላይ የመውሊድን በአል እያከበሩም ሀሳባቸው ለሀገራቸው ክብርና ለወገናቸው ህልውና ሲሉ ከዘመቱ ወገኖች ጋር ነው።
እኛ ከሞቀ ቤታችን ተቀምጠን መውሊድን ስናከብር ልጆቻችን ግን ግንባር ላይ ከጠላት ጋር ተፋጠዋል የሚሉት ግለሰቧ በአሉን ስናከብር እነርሱንና በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖችን በማሰብ ሊሆንም ይገባል ሲሉ ይናገራሉ።
ሀገር የምታድገውና ሰላሟን የምታገኘው እርስ በርስ ስንዋደድና ስንተባበር ነው በማለትም ልዩነትን ትቶ ለአንድ ሀገር ሰላም መነሳት ያስፈልጋል ይላሉ።
በብሔርና በሃይማኖት ሰበብ ለመከፋፈል የሚፈልጉ የውጭ ሀይሎችም ጆሮ ባለመስጠት አንድነታችንን እና ታላቅነታችንን ማሳየት ይኖርብናል ሲሉ ይመክራሉ።
በቤታቸውም ሆነ ግንባር ድረስ ዘምተው ለሚገኙ ሙስሊሞች እንኳን ለ1496ኛው የመውሊድ በአል አደረሳችሁ ብለዋል።
በሙሉጌታ ደሴ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!