አቶ ሽመልስ አብዲሳ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) እንኳን ለ1 ሺህ 496 ኛው የመውሊድ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ መልዕክት አስተላለፉ።
መውሊድ የነቢዩ መሐመድን መልካም ስራዎችን በማሰብ፣ ከመንገድ የወጣውን በማቃናት እና በማስተካከል የሚከበር ነው ብለዋል።
እኔም ይህንን ታስቦ የሚውለውን ታላቅ በዓል አስመልክቶ ለእስልምና እምነት ተከታዮች መልዕክቴን ሳስተላልፍ በታላቅ ትህትናና ደስታ ነው ብለዋል።
መውሊድ ሲታሰብ ነብዩ መሐመድ ምድር ላይ በኖሩባቸው ዓመታት የሰው ልጅ ክፋት እንዳያስብ፣ የሰውን እንዳይመኝ፣ሀቅን እንዳያጣምም፣እንዲተሳሰብ፣ የታረዘን እንዲያለብስ ፣ የተራበን እንዲያበላ የተጠማን እንዲያጠጣ በተግባርም ጭምር አሳይተው ያስተማሩትን በማስታወስ እንደሚከበር የእምነቱ አባቶች ያስተምራሉ።
የመረዳዳት እና ለተቸገረ ደራሽነታችን እሴት በመውሊድ ቀን ብቻ ሳይሆን የእለት ተግባራችን እና በትውልድ ቅብብሎሽ መሀል የሚቀጥል መሆኑ ይታመናል ብለዋል በመልዕክታቸው።
ይህ እሴት ከእምነቱ ተከታዮች ተሻግሮ፣ በሰፊው ህዝብ ውስጥ ማየትና በእለት ተዕለት የህይወት መመዘኛ ጀረጃ ላይ ደርሷል ያሉት አቶ ሽመልስ፥ ከዚህ አልፎ ህዝቡ በችግር ጊዜ የሚረዳዳበት እና አለኝታ የሚሆንበት ባህል ሆኗል ሲሉ በመልዕክታችው አስፍረዋል።
የዘንድሮውን በዓል ስናከብር ያለንን የዳበረ ባህል እና እሴት በማስታወስ ፣ ያጋጠመንን የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ችግር ውስጥ ለመውጣት እንተጋገዝ ሲሉ በዚህ አጋጣሚ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
የክልላችን እና የሀገራችን ህዝቦች በችግር ጊዜ ለወንድሞቻችሁ እና ለጎረቤቶቻችሁ ላደረጋችሁት ድጋፍ እና አለኝታነት በኦሮሚያ ክልል መንግስት ስም ያለንን ክብርና ምስጋና ላቀርብ እወዳለሁ ብለዋል።
በመጨረሻም በዓሉ የሰላም፣ የደስታ፣ የብልጽግና ይሁንላችሁ እያልኩ ፥ ከትናንቱ ይልቅ ዛሬ የመረዳዳት፣የመተዛዘን እና በጋራ መስራት የሚያስፈልግበት ወቅት መሆኑን ላስታውስ እወዳለሁ ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ሽመልስ አብዲሳ።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!