Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የገጠሟትን ችግሮች በራሷ አቅም ከመፍታት የሚያግዳት መሰናክል የለም-ዶ/ር ማመዱ ታንጋራ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ)”ኢትዮጵያ የገጠሟትን ችግሮች በራሷ አቅም ከመፍታት የሚያግዳት መሰናክል የለም” ሲሉ የጋምቢያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ማመዱ ታንጋራ ገለጹ።

ለሁለት ቀናት በአዲስ አበባ የተካሄደው 39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ ትናንት የተጠናቀቀ ሲሆን ÷በምክር ቤቱ ውይይት ላይ የአፍሪካ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችና ተወካዮች ተሳትፈዋል።

ከስብሰባው ተሳታፊዎች መካከል የጋምቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ማመዱ ታንጋራ በአዲስ አበባ እንጦጦ ፓርክ ጉብኝት አድርገዋል።

በዚሁ ጉብኝታቸው ላይ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ “ኢትዮጵያ ችግሮቿን በራሷ አቅም ከመፍታት የሚያግዳት መሰናክል የለም” ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር የነበረውን የቆየ ችግር የፈታችበትን መንገድ በማሳያነት ጠቅሰው፤ የራሷን ችግር የማትፈታበት ምንም አይነት ምክንያት የለም ብለዋል።

የአፍሪካ አገራት ያሉባቸውን ችግሮች በራሳቸው የመፍታት አቅማቸውን ሊያዳብሩ ይገባል ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ “ሌሎች በእኛ ጉዳይ ከእኛ በልጠው ስለ ራሳችን ሊነግሩን አይችሉም” ብለዋል።

በአፍሪካ ጉዳይ ከአፍሪካዊያን በላይ መፍትሄ የሚያመጣ አካል ሊኖር አይችልም የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረው “አፍሪካን ለመለወጥ ቆርጠው የተነሱ መሪዎች አሏት፤ አፍሪካ በትክክለኛው መንገድ እየተጓዘች ነው” ሲሉም ገልጸዋል።

“ኢትዮጵያና ጋምቢያ ያላቸው ግንኙነት በጣም ጥሩ የሚባል ነው” ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ትብብራቸውን ማጠናከር የሚያስችላቸው ስምምነቶች ከዚህ ቀደም መፈራረማቸውን አስታውሰዋል።
የሁለቱ አገራት ግንኙነት ከፍ ወዳለ ደረጃ እንደሚደርስ ያላቸውን እምነት በመግለፅ ስምምነቶቹን ወደ ተግባር ለመቀየር የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።
በጉብኝታቸው ኢትዮጵያ በፈጣን ልማት ላይ መሆኗንና የመላ አፍሪካዊያን ሁለተኛ ቤት አዲስ አበባም ትልቅ ለውጥ ላይ ትገኛለች ብለዋል ዶክተር ማመዱ።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.