Fana: At a Speed of Life!

ሕብረቱ በቅርቡ በኢትዮጵያ ላይ ያሳለፈው ውሳኔ ተቀባይነት የለውም – አቶ ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ)የአውሮፓ ሕብረት በቅርቡ በኢትዮጵያ ላይ ያሳለፈው ውሳኔ አድሏዊ እና ተቀባይነት የሌለው ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ተናገሩ።
አቶ ደመቀ ይህን ያሉት÷ ከስሎቫኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንዞ ሎጋር በስልክ በተወያዩበት ወቅት ነው፡፡
በውይይታቸውም÷ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ወቅታዊ ሁኔታ እና የኢትዮጵያ መንግስት ለትግራይ ክልል ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረስ እየተደረገ ስላለው ጥረት አቶ ደመቀ አብራርተውላቸዋል።
በአማራና በአፋር ክልሎች ህወሓት ያደረሰውን ጥቃትና በሁለቱ ክልሎች የንጹሃን ዜጎችን ህይዎት እንዲሁም ኑሮ እንዴት እንዳመሰቃቀለ በዝርዝር አስረድተዋል።
ትህነግ ወደ ትግራይ የሰብዓዊ እርዳታን ለማድረስ የገቡትን ከ20 በላይ የጭነት መኪናዎች ለወታደራዊ ዓላማ ማዋሉንም ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ሰባትየተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሠራተኞችን ከኢትዮጵያ ለቀው እንዲሄዱ ያደረገበትን ምክንያትም አብራርተውላቸዋል፡፡
በአውሮፓ ህብረት ፓርላማ በቅርቡ የተላለፈው ውሳኔ መሬት ላይ ያሉትን እውነታዎች ያላገናዘበ እና አድሎዓዊ በመሆኑ ተቀባይነት እንደሌለው ተናግረዋል፡፡
ህወሓት እየሄደበት ያለውን ትግል እና በዜጎች ላይ የሚያደርሰውን ጥቃት እንዲያቆምም አቶ ደመቀ ጠይቀዋል፡፡

የስሎቬኒያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንዜ ሎጋር በበኩላቸው÷ ሀገራቸው የወቅቱ የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር እንደመሆኗ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የሰብአዊ ሁኔታ እና እየተካሄደ ያለው ግጭት የሚያሳስባት መሆኑን ን ገልጸዋል።

 

አያይዘውም የተመድ ሠራተኞች ከኢትዮጵያ እንዲወጡ መደረጉ በሰብአዊ ድጋፍ እንቅስቃሴዎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳይፈጥር ያላቸውን ስጋት መግለጻቸው ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.