ኢትዮጵያ ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ሆና ትቀጥላለች ተባለ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ለተለያዩ ባለሃብቶች ምቹ ና ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ሆና እንደምትቀጥል ተገለጸ።
ከ40 በላይ የተለያዩ የውጭና የአገር ውስጥ ኩባንያዎች የተሳተፉበት የኢትዮጵያ የግብርና፣ ምግብና መጠጥ ማቀነባበርና የፕላስቲክ ህትመት የንግድ ትርኢት በአዲስ አበባ ተከፍቷል።
የንግድ ትርኢቱ ከዛሬ ጀምሮ ለተከታታይ ሶስት ቀናት በአዲስ አበባ ስካይ ላይት ሆቴል የሚከናወን ይሆናል።
የፕራና የኩነት ማኔጅንግ ዳይሬክተር አቶ ነብዩ ለማ፥ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ በማምረት የውጭ ምንዛሬን ለማዳን ኩነቱ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
በንግድ ትርኢቱ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ11 የተለያዩ አገራት የተውጣጡ 44 ኩባንያዎች መሳተፋቸውን ተናግረዋል።
ከተለየያዩ አገራት ተሳታፊ አምባሳደሮች የቅርብ ጊዜ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለመጠቀም የሚያስችል ልምድ ለመለዋወጥ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
የቱርክ አምባሳደር ያፕራክ አልፕ፤ የንግድ ትርኢቱ መካሄዱ የንግድ ተደራሽነትንና ኢንቨሰትመንትን ይበልጥ ለማሳደግ ይረዳል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ የቱርክ ባለሀብቶች ቀዳሚ ተመራጭ አገር መሆኗን ጠቅሰው የንግድ ግንኙነቱ የሁለቱን አገራት የጋራ ተጠቃሚነት የሚያሳድግ መሆኑንም ተናግረዋል።
የጀርመን አምባሳደር ስቴፈን ኢዩር የኢትዮጵያ ጀርመን የንግድ ትብብር ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ መሆኑን ተናግረዋል።
የንግድ ትርኢቱ በተለያዩ የንግድ ስራ ላይ ለተሰማሩ ባለሀብቶች የንግድ ሰንሰለት ውስጥ የመግባት እድል የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አምራቾች ያሉባቸውን ጉድለቶች ለመሙላት የሚያስችል ልምድ የሚገኝበት መሆኑንም ነው የገለጹት።
4ኛው የኢትዮጵያ የግብርና፣ ምግብና መጠጥ ማቀነባበርና የፕላስቲክ ህትመት የንግድ ትርኢት ከ2 ሺህ 500 በላይ ሰዎች ይጎበኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ኢዜአ ዘግቧል።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!