ኢትዮጵያ አሁን የገጠሟትን ችግሮች ወደ መልካም አጋጣሚ ለመቀየር መዘጋጀት ያስፈልጋል ተባለ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 3፣ 2014 (ኤፍ ቢሲ) ኢትዮጵያ አሁን የገጠሟትን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ወደ መልካም አጋጣሚ በመቀየር የአዲስ ተሿሚዎች ዋነኛ ተግባራቸው መሆን እንዳለበት የኪነ-ጥበብና የሚዲያ ባለሙያዎች ተናገሩ።
የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዮናታን ተስፋዬ እና የኢትዮጵያ ፊልም ሰሪዎች ማህበር ፕሬዚዳንት አርቲስት ደሣለኝ ሃይሉ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ÷ ኢትዮጵያ በታሪኳ የመጀመሪያ ተብሎ ሊጠቀስ የሚችል ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ አካሂዳ በህዝብ ተቀባይነት ያገኘ የመንግስት ምስረታ ማካሂዷን ገልጸዋል፡፡
በመንግስት ምስረታ ሂደትም ከዚህ ቀደም ባልተለመደ መልኩ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ከፍተኛ ቦታ ማግኘታቸው ኢትዮጵያ የጀመረችው የለውጥ ሂደት በአጭር ጊዜ ውስጥ ግቡን እንዲመታ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፊልም ሰሪዎች ማህበር ፕሬዚደንት አርቲስት ደሣለኝ ሃይሉ እንዳለው÷ አዲስ የተሾሙ ሚኒስትሮች የኢትዮጵያን ሰላምና ደህንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ማረጋገጥ ዋነኛ ተግባራቸው ሊሆን ይገባል፡፡
የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት በማስጠበቅ ሉዓላዊነቷ ተከብሮና በማንም ሊደፈር የማይችል አገር በመገንባት ላይም ትኩረት ሊያደርጉ እንደሚገባ አሳስቧል፡፡
የዜጎች መፈናቀል፣ ሞትና የንብረት ውድመት እንዲቆም እንዲሁም ግጭቶች እንዲወገዱ ከከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ብዙ ስራ ይጠበቃልም ብሏል፡፡
የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዮናታን ተስፋዬ በበኩላቸው÷ በኢትዮጵያ የተጀመረው የለውጥ ሂደት በበርካታ ተግዳሮቶች ታጅቦም ቢሆን ስኬቶችን እያስመዘገበ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የለውጥ ሂደቱ የታሰበለት ዓላማ ተሳክቶ የዜጎችን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዘርፎች ተጠቃሚ ለማድረግ ሁላችንም የሚጠበቅብንን ሃላፊነት ልንወጣ ይገባል ብለዋል፡፡
አዲስ ተሿሚዎች ኢትዮጵያ አሁን የገጠሟትን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ወደ መልካም አጋጣሚ በመቀየር ህዝቡን ተጠቃሚ የማድረግ ታላቅ ሃላፊነት የተጣለባቸው መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!