ተፎካካሪ ፓርቲዎች በመንግሥት ኃላፊነት ቦታዎች እንዲሳተፉ መደረጉ የመጠላለፍ የፖለቲካ ምዕራፍን ይዘጋል- አቶ አባዱላ ገመዳ
አዲስ አበባ፣ጥቅምት 3፣2014 (ኤፍ ቢሲ) ተፎካካሪ ፓርቲዎች በየደረጃው ባሉ የመንግሥት ኃላፊነት ቦታዎች ውስጥ እንዲሳተፉ መደረጉ ያለፈውን የመጠላለፍ ፖለቲካ ምዕራፍን ዘግቶ አዲስ የመተባበር መንፈስ እንደሚፈጥር አቶ አባዱላ ገመዳ ገለጹ።
አቶ አባዱላ ገመዳ እንዳሉት የተፎካካሪ ፓርቲ አባላት በየደረጃው ባሉ የመንግሥት ኃላፊነት ቦታዎች ውስጥ እንዲሳተፉ መደረጉ ያለፈውን የመጠላለፍ ፖለቲካ ምዕራፍ ዘግቶ ወደ አዲስ የመተባበር ምዕራፍ የሚያሸጋግር የፖለቲካ ባህል የፈጠረ ነው።
ብዙ ዘመናችን የተቃጠለው አዲስ ነገር በመፍጠር፣ ወደፊት በመራመድና በመተጋገዝ ሳይሆን በተለያዩ ሰበቦች አንዱ ሌላውን እያሳደደ ነው ያሉት አቶ አባ ዱላ ይህን አልፈን ወደ ትብብር ስንመጣ ለመጠላለፍ የምናጠፋውን ጊዜ፣ መዋዕለ ንዋይና ዕውቀት አገራችንን ወደፊት ለማሸጋገር እንደሚያግዝም ተናገረዋል።
ሂደቱ ቀደም ብለን ከለመድነውና ከምናውቀው ወጣ ባለ መንገድ የሀሳብ ልዩነት የታየበት እና በመሰባሰብና በመተባበር እንጂ በመለያየት አገርን ወደፊት ማራመድ እንደማይቻል በግልጽ የታየበት መሆኑንም አባ ዱላ ጠቁመዋል።
እንደ አቶ አባዱላ ገለጻ፤ የከዚ ቀደም ልምዳችን አገርን በማስቀደም መፎካከርና የሀሳብ ልዕልና ያለው ወደፊት እንዲመጣ መንገድ መክፈት ሳይሆን በጠላትነት በመፈረጅ አንዱ ሌላውን እስካልጣለ፣ እስካላፈረሰና እስካላጠፋ ድረስ የማይቀጥልበት የፖለቲካ ባህል ነበር ማለታቸዉን ኢ ፕ ድ ዘግቧል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!