ባህሬን ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለችውን ሪፎርም እንደምትደግፍ ገለጸች
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ)የባህሬን የገንዘብና የብሔራዊ ኢኮኖሚ ሚኒስትር ባህሬን ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለችውን ሪፎርም እንደምትደግፍ ገለጹ፡፡
በባህሬን የኢትዮጵያ የቆንስላ ጄነራል ጽህፈት ቤት መሪ አምባሳደር ጀማል በከርከባህሬን የገንዘብና የብሔራዊ ኢኮኖሚ ሚኒስትር ሼክ ሰሊማን ቢን ከልፋ አልካልፋ ጋር የሁለትዮች የኢኮኖሚ፣ የኢንቨስትመንት፣ የንግድ እንዲሁም ሁሉን አቀፍ ትብብር በሚጠናከርበት ላይ ተወያይተዋል፡፡
አምባሳደሩ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ሪፎርም አብራርተውላቸዋል፡፡
ከመካከለኛው ምስራቅ ጋር ያለንን ትብብር ለማጠናከር ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴ እየተደረገ ስለመሆኑም ነው የገለጹት፡፡
ኢትዮጵያ ሃገር አቀፍ የኢኮኖሚ ፕሮግራም ነድፋ እየሰራች መሆኑን ጠቁመው÷ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ማነቆ የሆኑትን ህግና አሰራር በመፈተሽ ለኢንቨስተሮች የተመቸች ሀገር እንድትሆን እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ትላልቅ የልማት ፕሮጀክቶችን ፕራይቬታይዝድ በማድረጓና ጥሩ አመራር በመሰጠቱ ይበልጥ ኢኮኖሚው ተነቃቅቷልም ነው ያሉት፡፡
ሼክ ሰሊማን ቢን ከልፋ አልካልፋ በበኩላቸው÷ በኢትዮጵያ ህዝቦች ይሁንታ ያገኘው ዲሞክራሲያዊ መንግስት ምስረታ በጥሩ ሁኔታ በመጠናቃቁ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለውን ሪፎርም ለማጠናከር የባህሬን መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር ያደርጋል ብለዋል፡፡
አያይዘውም የኢትዮጵያ ዜጎች ለባህሬን ኢኮኖሚ እድገትና ቀጣይነት እያበረከቱ ያለውን ሚና አድንቀው÷ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ለአቻቻው አቶ አህመድ ሺዴ የየገንዘብ ሚኒስትር ሆነው በድጋሜ በመሾማቸውም እንኳን ደስያለዎች ብለዋል፡፡
ሁለቱ ኃላፊዎች በቀጣይ የሁለቱ ወንድማማች ሃገራት ግንኙነትና ትብብር ይበልጥ በሚጠናከርበት ዙሪያ ተቀራርበው ለመስራት የጋራ መግባባት ላይ መድረሳቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!