ኢዜአ ከፀሀይ አሳታሚ ድርጅት በጋር የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ ተፈራረመ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 28፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ከፀሀይ አሳታሚ ድርጅት በጋራ መስራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ ተፈራረመ።
ስምምነቱን የኢዜአ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ እና የጸሐይ አሳታሚ ድርጅት መስራችና ባለቤት አቶ ኤልያስ ወንድሙ ተፈራርመዋል፡፡
ስምምነቱም ተቋማቱ የሀገር ግንባታ ስራዎችን በቅንጅት እንዲያከናውኑ የሚያሥችል መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
የፀሀይ አሳታሚ ድርጅት መስራችና ባለቤት አቶ ኤልያሥ ወንድሙ በዚህን ወቅት ኢዜአ በኢትዮጵያ የሚዲያ ታሪክ ውስጥ ረዥም እድሜ ያስቆጠረና በዘርፉም የካበተ ልምድ ያለው ተቋም መሆኑን ተናግረዋል።
ስምምነቱ የኢዜአ ስራዎችን በውጭ ሀገር ተደራሽ በማድረግና በውጭ ያሉ መረጃዎች ደግሞ ለተቋሙ በማድረስ የኢትዮጵያን ገጽታ ለመገንባት ድልድይ ሆኖ እንደሚያገለግልም አንስተዋል።
በተጨማሪ በሁለቱ ተቋማት መካከል ያለውን ትብብር በተቀናጀ መልኩ በማጠናከር ወደ ተሻለ ምእራፍ እንዲሸጋገር እንደሚያግዝም ነው የተናገሩት።
ስምምነቱ የዲያስፖራው ማህበረሰብ ኢትዮጵያ ላይ የተከፈተውን የሀሰት ዘመቻ ለመቀልበስ እያከናወነ ያለውን ጥረት በተደራጀ መረጃ ለማገዝ እንደሚጠቅምም አቶ ኤሊያስ ተናግረዋል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያን መልካም ግጽታን ለማስተዋወቅ የሚደረገውን ጥረት ያግዛል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ በበኩላቸው የፀሀይ አሳታሚ ድርጅት የሚያከናውናቸው ተግባራት ከኢዜአ ተልዕኮ ጋር ተቀራራቢነት እንዳላቸው ገልጸዋል።
አሳታሚ ድርጅቱ በሀገር ግንባታ ስራዎች ላይ በስፋት እየተሳተፈ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዚህ አቋያ ስምምነቱ ኢዜአ የሚሰራቸው የሀገር ገጽታ ግንባታ ስራዎች በስፋት ተደራሽ እንዲሆኑ እንደሚያግዝ ገልጸዋል፡፡
ሁለቱ ተቋማት ተቀናጅተው መስራታቸው የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ተግባራት በማገዝ ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑንም ነው የተናገሩት።
በተለይ አንዳንድ የምዕራባዊያን አገራት በኢትዮጵያ ላይ የከፈቱትን የሀሰት ዘመቻ ለመቀልበስ የሚያስችል መረጃ ለመለዋወጥ ስምምነቱ አጋዥ መሆኑንም መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ስምምነቱ የተጀመረው ሀገራዊ ለውጥ የበለጠ እንዲጠናከር በማገዝ ኢትዮጵያን አትራፊ እንደሚያደርጋትም ዋና ስራ አስፈጻሚው አቶ ሰይፈ ደርቤ ጠቁመዋል፡፡
ፀሀይ አሳታሚ ድርጅት በአሜሪካ የሚገኝ ተቋም ሲሆን፤ የኢትዮጵያን ታሪክ፣ ባህልና እሴቶችን የሚያስተዋውቁ መጽሃፍትን አሳትሞ ከማሰራጨት ጀምሮ የሀገር ግንባታን የሚያጎለብቱ ተግባራት ላይ ትኩረቱን አድርጎ ይሰራል።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!