ተቋማት በሶሻል ሚዲያ አጠቃቀም ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ አድርጉ- ኢመደኤ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 28፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያና የህዝቦቿ ጠላቶችና ተባባሪዎቻቸው ከውስጥና ከውጭ ሆነው የሳይበር ምህዳሩን በመጠቀም በተለያዩ የመሰረተ ልማትና የመረጃ አውታሮች ላይ ቀጥተኛ ጥቃት ለመፈጸም እያደረጉት ያለው ሙከራ አለመሳካቱን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ገለጸ፡፡
ኢትዮጵያ እያከናወነች ባለችው ከህግ ማስከበርና የህልዉና ዘመቻ ጋር እንዲሁም ሌሎች ቀጠናዊና አለምአቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታዎች ጋር በተያያዘ በሳይበር ምህዳሩ ላይ እየታዩ ያሉት አዝማሚያዎችና ሙከራዎቻቸውን ማሳሰብና ማሳውቅ አስፈልጓል ብሏል ኤጀንሲው፡፡
እነዚህ እኩይ ዓላማ ያላቸው አካላት ሀገር ዉስጥ ሆነው የመሰረተ-ልማትና የመረጃ አውታሮችን እንዲሁም ሲስተሞችን እንዲያስተዳደሩ በተቋማት መብት የተሰጣቸውን (ሲስተም አድሚኒስ) ለሙያቸው፣ ለተቋማቸውና ለሀገራቸው ታማኝ ያልሆኑ ጥቂት ጡት ነካሽ ባንዳዎችን በመጠቀምና እክል ለመፍጠር እየሰሩ ነው ብሏል፡፡
ማንኛዉንም የመሰረተ ልማትና የመረጃ አውታሮችን እንዲሁም ሲስተሞችን የምታስተዳደሩ መንግስታዊም ሆነ መንግስታዊ ያልሆናችሁ ተቋማት÷ ሲስተሞችን እንዲያስተዳደሩ መብት የተሰጣቸው ወይም የተቋማትን የሶሻል ሚዲያ አካውንቶችን እንዲያስተዳድሩ የይለፍ-ቃል (ፓስወርድ) እንዲይዙ የተፈቀደላቸው ግለሰቦችና ቡድኖች ወይም (ሲስተም ወይም ኔትወርክ አድሚንስ) ትክክለኛውን የሙያ ብቃት እና ጥብቅ የስነ ምግባር ማጣራት የተደረገባቸው መሆኑን ደጋግማችሁ እንድታረጋግጡ ሲል ማሳሰቡን ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!