ማሪያ ሬሳ እና ድሚትሪ ሙራቶቭ የ2021 የሠላም ኖቤል ሽልማት አሸናፊዎች ሆኑ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 28፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ፊሊፒንሳዊቷ ማሪያ ሬሳ እና ሩሲያዊው ድሚትሪ ሙራቶቭ የ2021 የሠላም ኖቤል ሽልማት አሸናፊዎች ሆኑ፡፡
ያሸነፉትም ዴሞክራሲና ሠላም ይሰፍን ዘንድ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት እንዲከበር ባበረከቱት አስተዋጽዖ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
ፊሊፒናዊዋ ማሪያ ሬሳ እና ሩሲያዊው ድሚትሪ ሙራቶቭ÷ የዓለም ጋዜጠኞች ለዴሞክራሲ እና ፕሬስ ነፃነት የሚያደርጉትን ትግል ወክለውም እየተንቀሳቀሱ ነው ተብሏል፡፡
ማሪያ ሬሳ÷ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብቷን በወኔ እና በድፍረት በመጠቀም ሥልጣንን ያለ አግባብ መጠቀም፣ ሁከት ማስነሳት እና በሀገሯ እያገነገነ የመጣው ፈላጭ ቆራጭነት ያስከተለውን ቀውስ ማጋለጧ ተጠቁሟል፡፡
ማሪያ ሬሳ÷ በፈረንጆቹ 2012 “ራፕለር” የተሰኘ የዲጂታል ሚዲያ ኩባንያ በጥምረት መስርታ የምርመራ ጋዜጠኝነት ላይ ኃላፊ በመሆን እየሠራችም ነው ተብሏል፡፡
ድሚትሪ ሙራቶቭ ደግሞ÷ የሩሲያ ፈታኝ ሁኔታ ሳይበግረው ሐሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት እንዲከበር ከፍተኛ አስተዋፅዖ አበርክቷል ነው የተባለው፡፡
ድሚትሪ ÷ በፈረንጆቹ 1993 “ኖቫታ ጋዜታ” ተብሎ መታተም በጀመረው ገለልተኛ ጋዜጣ ውስጥ ከመስራቾቹ አንዱ ነው፡፡
ከፈረንጆቹ 1995 ጀምሮ የጋዜጣው የአርትዖት ክፍል ኃላፊ በመሆንም ለ24 ዓመታት አገልግሏል፡፡
በአሁኑ ጊዜም “ኖቫታ ጋዜታ” የተባለው የጋዜጣ ሕትመት በሩሲያ ውስጥ ከመንግስት አቋም ገለልተኛ መሆኑ የተመሰከረለት እና እውነት ላይ የተመሰረተ መረጃ በማውጣት የታወቀ መሆኑን ከኖቤል ሽልማት ገፅ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡