የ2021 የኬሚስትሪ ኖቤል ሽልማትን ሁለት ሣይንቲስቶች በጋራ አሸነፉ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ)በስዊድን ስቶኮልም “ሮያል ሣይንስ አካዳሚ” የተሰየመው የኖቤል ሽልማት ጉባዔ የ2021 የኬሚስትሪ ዘርፍ የኖቤል ሽልማት ለጀርመናዊው ሣይንቲስት ቤንጃሚን ሊስት እና ለአሜሪካዊው ዴቪድ ማክሚላን በጋራ ሸለመ፡፡
የኖቤል ኮሚቴው ÷ ሣይንቲስቶቹ የተሸለሙት በፋርማሲ ውስጥ በሚደረጉ ጥናቶች ለሞለኪውል ግንባታ ሲውል የነበረ “ኦርጋኖ ካታሊሲስ” የተሰኘ ትክክለኛለቱ ከፍተኛ የሆነ አዲስ ቁስ በማበልፀጋቸው ነው ብሏል፡፡
ሁለቱም ሳይንቲስቶች ዕድሜያቸው 53 ሲሆን÷ ለሽልማት የቀረበላቸውን 1 ነጥብ 1 ሚሊየን ዶላር ለሁለት እንደሚካፈሉ ነው የተገለጸው፡፡
ማክሚላን አሜሪካ ውስጥ በሚገኘው ፕሪንስተን ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ፕሮፌሰር ሆኖ እያገለገለ የሚገኝ ሲሆን÷ ሊስት ደግሞ በጀርመን ማክስ ፕላንክ ኢንስቲትዩት ውስጥ በዳይሬክተርነት እየሠራ መሆኑን ሲጂቲኤን ዘግቧል፡፡
በዓለማየሁ ገረመው