ኤጀንሲው ከ187 ሚሊየን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው አጎበሮችን እያሰራጨ ነው
አዲስ አበባ፣ ጥር 28፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ 187 ሚሊየን 395 ሺህ ብር ዋጋ ያላቸውን 3 ነጥብ 1 ሚሊየን አጎበሮች ማሰራጨት መጀመሩን አስታወቀ።
በኤጀንሲው የመድኃኒትና የህክምና መገልገያዎች ስርጭትና ተሽከርካሪ ስምሪት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አህመድ ከድር፥ ኬሞኒክስ ከተሰኘው ድርጅት ጋር በመተባበር ለሶስት ክልሎች አጎበር የማሰራጨት ስራ መጀመሩን ተናግረዋል።
ዳይሬክተሩ አንድ አጎበርም ሆነ የሚረጨው ኬሚካል ለሶስት ዓመት ብቻ የሚያገለግል መሆኑን አስታውሰዋል።
በዚህ መሰረት በአሁኑ ወቅት ከ3 ዓመት በፊት የተሰራጩትን አጎበሮች መቀየር የሚያስችል ስርጭት እየተካሄደ መሆኑን ነው የገለጹት።
ስርጭቱ ካሳለፍነው ሳምንት ጀምሮ በደቡብ ክልል በሚገኙት ሠገን፣ ወላይታ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ሸካ እና ጋሞ ጎፋ ዞኖች እየተካሄደ መሆኑንም አስረድተዋል።
የአጎበር ስርጭቱ የመጀመሪያ ዙር መሆኑን ያነሱት ዳይሬክተሩ፥ በቀጣይ ወራት በቀሪ የደቡብ፣ ቤኒሻንጉል እና ጋምቤላ ክልሎች ይቀጥላል ብለዋል።