የኮሮና ቫይረስን በመስጋት የሰርግ ስነ ስርዓታቸውን በቀጥታ ስርጭት የተከታተሉት ጥንዶች
አዲስ አበባ፣ ጥር 28፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) መነሻውን ከወደ ቻይና ያደረገው የኖቭል ኮሮና ቫይረስ ዓለም አቀፋዊ ስጋት ከሆነ ውሎ አድሯል።
የቫይረሱ ስርጭትም አድማሱን እያሰፋ የበርካቶችን ህይዎትም እየቀጠፈ ይገኛል።
ከሰሞኑ የቫይረሱን ስርጭት በመፍራት ከወደ ሲንጋፖር የተሰማው ዜና ደግሞ መነጋጋሪያ ሆኗል።
ለመጋባት ቀናት የቀራቸው ፍቅረኛሞች ቫይረሱን ፍራቻ የሰርግ ስነ ስርዓታቸውን በቀጥታ ስርጭት መከታተላቸው ተሰምቷል።
እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱት ደግሞ ልክ እንደ ቻይናዋ ውሃን ከተማ የቫይረሱ መነሻ በሆነች መንደር ጉብኝት ካደረጉ በኋላ ነው ተብሏል።
ወደ ስፍራው ካቀኑ በኋላም ለ14 ቀናት ያክል ራሳቸውን በማግለል በልዩ ማቆያ ክፍል ውስጥ መቆየትን መርጠዋል።
በዚህ መሃል እያሉ የሰርግ ቀናቸው ይደርሳል፥ በሰርግ ስነ ስርዓቱ ላይ መገኘት አደጋ ያስከትላል በሚልም ሰርጉን ከመሰረዝ ሌላ አማራጭ መፍትሄ ይፈልጋሉ።
በዚህም ከተጋባዥ እንግዶቹ ጋር በአካል ሰላምታ ለመለዋወጥም ሆነ በቅርብ ርቀት ለመገናኛት ባይታደሉም ሰርጉ በተከናወነበት ሆቴል ውስጥ በተገጠመ መሳሪያ ወዳጅ ዘመድ የተገኘበትን የሰርግ ስነ ስርት በቀጥታ መከታተል ችለዋል።
ሙሽሮቹ ሰርጋቸውን በቀጥታ እየተከታተሉ የደስታቸው ተካፋይ ለመሆን የመጡ እንግዶችን ይቅርታ ጠይቀዋል።
“በመካከላችሁ በመገኘት አስደሳች ጊዜ ባለማሳለፋችን እናዝናለን፤ በሰርጋችን ቀን ስለተገኛችሁ ግን እናመሰግናለን” ብለዋቸዋል እንግዶቹን በመልዕክታቸው።
ምንጭ፡-ኦዲቲ ሴንተራል