ህወሓት በ1981 እንዳደረገው በደላንታ አቋርጦ መሃል ሀገር የመግባት ፍላጎቱ አይሳካም – ብርጋዴል ጀነራል አለሙ አየነ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሽብር ቡድኑ ህወሓት ደቡብ ወሎን እንደ መሸጋገሪያ ተጠቅሞ አራት ኪሎ የረገጠበትን የ1981 አካሄድ ዛሬም ለመድገም ቢፍጨረጨርም በፍጹም ሊሳካለት አይችልም ሲሉ የደቡብ ዕዝ ምክትል አዛዥ ብርጋዴል ጀነራል አለሙ አየነ ገለጹ፡፡
ለዚህም በደላንታ ግንባር ተፅእኖውን ለማበርታት እና ሰብሮ ለማለፍ ያላደረገው ሙከራ የለም፤ ሊሳካለት አልቻለም እንጅ ነው ያሉት።
ከዚሁ ጋር በተገናኘ ከፋና ቴሌቭዥን ጋር ቆይታ ያደረጉት የግንበሩ ከፍተኛ አመራርና የደቡብ ዕዝ ምክትል አዛዥ ብርጋዴል ጀነራል አለሙ አየነ÷ ህወሓት በወቅቱ ለውጤት ያበቃውን አካሄድ በተሳሳተ ግምገማ ዛሬም ለመተግበር መሯሯጡን ቀጥሏል፤ እያስወራ ያለውም ይህንኑ ነው ብለዋል።
የደላንታን መሬት ከሰራዊቱና ከጦር መሪዎቹ እንዲሁም ከህዝቡ በላይ አያውቁትም ያሉት ብርጋዴር ጄኔራሉ÷ 1983 ህዝቡ ተሸክሞ እንዳስገባቸው ፈፅሞ ረስተውታል ብለዋል።
አካሄዳቸውን እናውቃለን ያሉት ብርጋዴር ጄኔራል አለሙ አየነ÷ ያኔም ቢሆን ጁንታው ተዋግቶ አሸንፎ ሳይሆን መሃል ሀገር የገባው ህዝቡ ተቀብሎ መንገድ እየመራ እያበላ እያጠጣ ልጆቹን እየመረቀ እየሰጠ ፍፁም ተባባሪ በመሆኑ ነበር ሲሉ ገልፀዋል።
አማራ ክልል ሲገባ የአማራ ህዝብ፣ ኦሮሚያ ሲገባ የኦሮሞ ህዝብ አይዞህ ብሎ ተሸክሞ እንዳስገባው ረስቶታልም ነው ያሉት።
እንደስሌታቸው ቢሆን ኖሮ አዲስ አበባ ገብተዋል ያሉት የደቡብ ዕዝ ምክትል አዛዥ ብርጋዴል ጀነራል አለሙ አየነ÷ ዛሬ ግን ከ1981 ዱ ሁኔታ ጋር የተመሳሰለ ነገር የለም፤ ቡድኑን መንገድ የሚያሳይ አቅፎ ደግፎ ሚያሳልፍ ልጁንም አሳልፎ የሚሰጥ ህዝብ የለም፤ እናም የተሳሳተ ግምገማው ዋጋ እያስከፈለው ነው ብለዋል።
ለደቡብ ወሎ ህዝብ ብቻ ሳይሆን÷ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ የሰጡት ግምትና ያሳዩት ንቀት ትልቅ ዋጋ እያስከፈላቸው ነው ብለዋል ብርጋዴር ጄኔራሉ።
ከሰራዊቱና ከህዝቡ በላይ አካባቢውን እና መውጫ መግቢያውን አያውቀውም እና ጁንታው በደላንታ ወገልጤና አቋርጦ መሀል ሀገር ይገባል የሚል ስጋት ፈፅሞ ሊኖር አይገባም፤ ለዚህም ህዝቡ ዋናው መተማመኛ ነው ብለዋል።
ቡድኑን ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመቅበር ቀሪ መልክ የማስያዝ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን እና ድል እንደሚመዘገብም ነው የደቡብ ዕዝ ምክትል አዛዥ ብርጋዴል ጀነራል አለሙ አየነ የገለፁት።
በሀብታሙ ተ/ስላሴና እሸቱ ወ/ሚካኤል
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!