Fana: At a Speed of Life!

የክቡር ዶክተር አርቲስት ለማ ጉያ ፋውንዴሽን ተመሰረተ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የጥበብ አበርክቷቸውን ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ የሚያስችል የክቡር ዶክተር አርቲስት ለማ ጉያ ፋውንዴሽን ተመሰረተ።

በምስረታው መድረክ አርቲስቱ የጻፏቸው ሶስት መጻህፍትም ተመርቀዋል።

ከልጅነት የሸክላ ቅርጻ ቅርጽ መነሻነት የአየር ሃይል መምህርነትና ታላቅ የአገር ፍቅር በመግለጽ የሚታወቁት እንዲሁም በፍየል ቆዳ ላይ በሚሰሩትና በልዩ ጥበብ እስከ ዓለም ሎሬትነት የደረሱት ክቡር ዶክተር አርቲስት ለማ ጉያን አበርክቶዎች ማስቀጠል የሚያስችል ፋውንዴሽን ዛሬ በይፋ ተመስርቷል።

በፋውንዴሽኑ ምስረታ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስትን በመወከል የተገኙት የክልሉ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ጌቱ ወዬሳ እንዳሉት÷ የክልሉ መንግስት የታላቁን አርቲስት ለትውልድ የሚያስተላልፉ ሰፊ ተግባራትን ከቤተሰቡና ከስራ ባልደረቦቹ ጋር በመሆን በመስራት ላይ ነው።

በዚህም ፋውንዴሽኑን ከማቋቋም ባለፈ በትውልድ ስፍራቸውና በጥበብ ምንጫቸው ቢሾፍቱ ከተማ በመንግስት ወጪ ሀውልታቸውን በማሰራት ላይ ነው፤ በኦሮሞ ባህል ማዕከል ደግሞ በስማቸው ሙዚየም ከፍቶላቸዋል።

እነዚህ ተግባራት ታዲያ ታላቁን የጥበብ ሰው ቢያንስባቸው እንጂ አይበዛባቸውም ነው ያሉት አቶ ጌቱ።

የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ አቶ ከበደ ዴሲሳ በበኩላቸው÷ ክቡር ዶክተር አርቲስት ለማ የአገራችን ብሎም የአፍሪካ ትልቁ የጥበብ ንጉስ ናቸው።

መላው የጥበብ ወዳጅ ሲያስታውሳቸውም በታላቅ የጥበብ አበርክቷቸው ነው ያሉት።

በመድረኩ ተገኝተው ስለ አባታቸው የጥበብ አበርክቶና ቀጣይ ስራዎች የተናገሩት ደግሞ የአርቲስት ለማ ጉያ ልጅ የሆኑት ወይዘሪት ሰላም ለማ ናቸው።

ወይዘሪት ሰላም “እኛ የለማ ቅርሶች ነን” በማለት ነው የአባታቸውን ራዕይና ቅርስ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ እየተጉ መሆናቸውን ያወሱት።

አርቲስቱ በተለየ ተሰጥኦ ከ1ሺህ በላይ የቆዳ ላይ የስዕል ጥበብ ማበርከታቸው የተወሳ ሲሆን÷ በእነዚያ አበርክቷቸውም በስማቸው ለማዊነት(Lemmism) የሚል ዓለም አቀፍ የሎሬት ማዕረግ እንደተጎናጸፉም በመድረኩ ተወስቷል።

በዚህም ከእረኝነት እስከ ለማዊነት(From Hearding to Lemmism) የስዕል ጥበብ ማስተማሪያ ያለ አስተማሪ የሚሉትና በአርቲስቱ የተደረሱ ሶስት መጻህፍት ተመርቀዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.