Fana: At a Speed of Life!

ወርሃዊ የቲክቶክ ተጠቃሚዎች ቁጥር 1 ቢሊየን አለፈ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 18፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ)የዛሬ አራት ዓመት ገደማ ባይትዳንስ በተሰኘው የቻይና ኩባንያ ይፋ የተደረገው ቲክቶክ የወርሃዊ ተጠቃሚዎቹ ቁጥር ከ1 ቢሊየን ማለፉን አስታውቋል፡፡

ይፋ ከተደረገበት ጊዜ አንስቶ በሚሰራጩበት በፖፕ ሙዚቃ የታጀቡ የዳንስ እንቅስቃሴዎች የተነሳ ቀድሞውንም ከፍተኛ ዕውቅናን እያገኘ የነበረው ቲክቶክ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መቀስቀስን እና ብዙዎችም ቤት ውስጥ መቀመጣቸውን ተከትሎ የተጠቃሚዎቹ ቁጥር በከፍተኛ መጠን ሊጨምር ችሏል፡፡

በመጀመሪያ የ15 ሴኮንድ ቪዲዮዎችን ብቻ ለማሳየት ብሎ የጀመረው ቲክቶክ በሂደት ግን ተጨማሪ ተጠቃሚዎችን ለማግኘት እና ከዩትዩብ ጋር ለመፎካከር እንዲያስችለው ይህን የጊዜ ገደብ ወደ ሦስት ደቂቃ ከፍ አድርጎታል፡፡

ታድያ የቲክቶክ ወርሀዊ ተጠቃሚዎች ቁጥር ከ1 ቢሊየን ይለፍ እንጂ ወርሃዊ ተጠቃሚዎቹ 2ነጥብ 3 ቢሊየን ከሆኑለት ዩትዩብ አንፃር ገና ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

የቲክቶክ ከፍተኛ ተቀባይነትን የተመለከተው ዩትዩብ በበኩሉ÷ ዩትዩብ-ሾርት የተሰኘ በተመሳሳይ አጫጭር ቪዲዮዎችን የሚያሰራጭ ገፅን ይፋ ያደረገ ሲሆን÷ ገፁ ከ100 በላይ ሃገራት ውስጥም እየሰራ ይገኛል፡፡

ቲክቶክ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ የተጠቃሚዎቹ ቁጥር እንዲህ መብዛቱን ተከትሎ ከዚህ ዕድል ይበልጥ ለመጠቀም እየሰራ ይገኛል፡፡

በዚህም ባለፈው የፈረንጆች ዓመት የማስታወቂያ ስራዎችን በይበልጥ መስራት የጀመረ ሲሆን÷ ከወር በፊትም ተጠቃሚዎች በማህበራዊ ሚዲያ ገፁ ላይ ቪዲዮ በሚያሰራጩ ሰዎች አማካኝነት የሚቀርቡ ምርቶችን በቀጥታ ለመግዛት እንዲችሉ የሚያደርግ ስርዓትን መዘርጋቱን ቴክስፕሎርን ጠቅሶ የቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት አስነብቧል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.