የመስቀል ደመራ በዓል በመላው ኢትዮጵያ ተከብሮ ዋለ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የመስቀል ደመራ በዓል በመላው ኢትዮጵያ ተከብሮ ውሏል፡፡
በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይም በዓሉ የተከበረ ሲሆን÷ በክብረ በዓሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴና የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሰዉ ተገኝተዋል፡፡
በክብረ በዓሉ መልዕክት ያስተላለፉት÷ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክስርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ መስቀል ከሁሉ ነገር በላይ ነው ያሉ ሲሆን ፥ የመስቀል ትርጉም ሰላም፤ ፍቅር፣ አንድነትና እርቅ ነው በማለትም አስረድተዋል።
ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው ÷የአገራችንን እውነት ሊጋርዱና ሊያጠለሹ የሚሞክሩ የውስጥና የውጭ ሃይሎች ሙከራ ቢያደርጉም የኢትዮጵያ እውነት እንደ ደመራው ብርሃን መድመቁ አይቀሬ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ መስቀል ጨለማን የገለጠ፥ የብርሃንን አሸናፊነት ያሳየ፤ አዲሰ ተስፋን ያበሰረ ከድንግዝግዝ ጨለማ ውስጥ አስደናቂ የሆነ ብርሃን መገኘት ማሳያ እንደሆነም አመልክተዋል።
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሰዉ÷ ከአባቶቻችን የተረከብነውን የመስቀል በዓልም ሃይማኖታዊ እሴቱን በመጠበቅ ለቀጣዩ ትውልድ ማሰተላለፍ እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡
በዓሉን ስናከበር የተሰጠንን ሃላፊነት በብቃት በመወጣት ሰላምና ፍቅርን በማስተማር ሊሆን ይገባል ፤ የምንወዳትን ታላቅ ሃገር ልዕልናዋን አስጠብቆ ለማቆየት በትጋት መስራት ይገባናል ሲሉም ሚኒስተሯ ተናግረዋል፡፡
በአደባባይ ከሚከበሩ በዓላት መከከል አንዱ የሆነው የመስቀል ደመራ በዓል በመላው ኢትዮጵያ በየዓመቱ መስከረም 16 በድምቀት ይከበራል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን