የፌስቡክ ካሜራ የተገጠመለት መነፅር
አዲስ አበባ፣ መስከረም 3፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ)እውቁ የማህበራዊ ድረ-ገጽ ፌስቡክ ካሜራ የተገጠመለት ልዩ መነፅር ሰርቶ ማቅረቡ ተሰማ፡፡
መነፅሩ ከታዋቂው የመነፅር አምራች ድርጅት ሬይ ባን እና የአውሮፓ ካምፓኒ ከሆነው ኢስሎርሊክሳቲካ ጋር በጥምረት የተሰራ እንደሆነ ሲገለፅ፣ ሰዎች በቀላሉ አድርገውት ሊጠቀሙበት ይችላሉ ነው የተባለው፡፡
በመነፅሩ ተጠቃሚዎች ፎቶዎችን በቀላሉ ማንሳት እንዲችሉ ተደርጎ የተሰራ እንደሆነ ተነግሮለታል፡፡
መነፅሩ ፎቶ ከማንሳት በተጨማሪ መናገሪያ እና ማዳመጫ የተገጠመለት ሲሆን÷ በዚህም ተጠቃሚዎች የስልክ መልዕክቶችን በቀላሉ መለዋወጥ ይችላሉ ተብሏል፡፡
በተጨማሪ መነፅሩ መተግበሪያ ያለው ሲሆን÷ ኃይል መሙላት የሚያስችለው ክፍልም ተዘጋጅቶለታል ነው የተባለው፡፡
መነፅሩ አሁን ላይ በአሜሪካ፣ በእንግሊዝ፣ በካናዳ፣ በአይርላንድና በአውስትራሊያ ለገበያ የቀረበ ሲሆን 299 የአሜሪካ ዶላርም በመሸጥ ላይ እንደሆነ ነው የተገለፀው፡፡
በጉዳዩ ላይ መረጃ የሰጠው ፌስቡክ መነፅሩ ሰዎች እያንዳንዱን እንቅስቃሴዎቻቸውን በምስል ማስቀረት እንደሚያስችላቸው ተናግሯል፡፡
ሙዚቃ ማዳመጥ፣ ስልክ ማነጋገር፣ ፌስቡክ መጠቀም እንዲሆም በማህበራዊ ሚዲያ ምስሎችንና ቪዲዮዎችን ለሰዎች ማጋራት ያስችላቸዋል ሲልም መግለፁን ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስትቲዩት ቴክስፕሎርን ጠቅሶ ያጋራው መረጃ ያመላክታል፡፡
ፌስቡክና ሬይ ባን የአውሮፓ ካምፓኒ ከሆነው ኢስሎርሊክሳቲካ ጋር በትብብር የሰሩት ይህ መነፅር ለገበያ ቀርቦ ጥቅም ላይ እንዲውል ለዓመታት የሚቆይ ህጋዊ የስምምነት ፊርማቸውን ማስቀመጣቸው ተጠቁሟል፡፡
ተጠቃሚዎች ሙሉ ቀን አድርገውት እየተጠቀሙበት ይውሉ ይሆን ? በቀጣይ አብረን የምናየው ይሆናል!