የፊፋው ፕሬዚዳንት የአፍሪካ ዋንጫ በ4 ዓመት አንድ ጊዜ እንዲካሄድ እንደሚፈልጉ ገለፁ
አዲስ አበባ ፣ ጥር 25፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ አስተዳዳሪ አካል /ፊፋ/ ፕሬዚዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ የአፍሪካ ዋንጫ ላይ የመርሃ ግብር ማስተካከያ እንዲደረግ እንደሚፈልጉ ገለፁ።
ፕሬዚዳንቱ በየሁለት ዓመቱ የሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ የእግር ኳስ ጨዋታ በ4 ዓመት አንድ ጊዜ እንዲካሄድ ፍላጎት አላቸው።
ኢንፋንቲኖ በሞሮኮ ራባት በእግር ኳስ እድገት እና መሰረተ ልማት ላይ ትኩረት በማድረግ እየተካሄደ ባለው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ስብሰባ ላይ የአፍሪካ ዋንጫ የመርሃ ግብር ማስተካከያ ላይ የውሳኔ ሀሳብ ማቅረባቸው ተነግሯል።
“የአፍሪካ ዋንጫ ከአውሮፓ ዋንጫ ጋር ሲነፃፀር የሚያገኘው ገቢ በ20 እጥፍ ያነሰ ነው፤ ይህ በገቢም ይሁን በመሰረተ ልማት ግንባታ ጥሩ አይደለም፤ ስለዚህ በየአራት ዓመቱ መካሄዱ ቢታሰብበት ጥሩ ነው” ሲሉም ተናግረዋል።
ቀጣዩ የአፍሪካ ዋንጫ በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2021 በካሜሩን አስተናጋጅነት የሚካሄድ ሲሆን፥ የ2019 የአፍሪካ ዋንጫ በግብፅ አስተናጋጅነት መካሄዱ ይታወሳል።
ፕሬዚዳንቱ ከአፍሪካ ዋንጫ መርሃ ግብር በተጨማሪ ፊፋ እና ካፍ በትኩረት የሚሰሩባቸው ሶስት ቁልፍ ስትራቴጂዎችንም ይፋ አድርገዋል።
በዚህም “ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ ማበጀትን፣ ሁለቱ ተቋማት በጋራ በሚሰሩባቸው፤ ዳኝነት፣ መሰረተ ልማት እና ውድድሮችን የተመለከተ ምክረ ሃሳባቸውን ነው ያቀረቡት።
በመሰረተ ልማት በኩል ፊፋ በእያንዳንዱ የፊፋ እና የካፍ አባል በሆኑ 54 ሀገራት ውስጥ በ1 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ስታዲየም እንደሚገነባ አስታውቀዋል።
በዚህ ፕሮጀክት ጥሩ ስታደየም ባለባቸው ሀገራት በበጀቱ ሌሎች እግር ኳስን የሚያሳድጉ የመሰረተ ልማት ስራዎች ይሰራሉም ነው ያሉት።
ምንጭ፦ africa.cgtn.com