በመዲናዋ ለበዓል የግብርና እና የኢንዱስትሪ የፍጆታ ሸቀጦች መቅረባቸው ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 28፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የዘመን መለወጫ በዓልን ምክንያት በማድረግ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶች ወደ ከተማዋ እንዲገቡ ከአምራቾች ጋር በመነጋገር ገበያውን ለማረጋጋት እየተሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሕብረት ሥራ ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሲሳይ አረጋ ገለፁ።
ገበያውን ለማረጋጋትም በፍጆታ አቅርቦት ረገድ አምራቾች፣ በከተማዋ በሚገኙ 148 መሠረታዊ የሸማቾች ሕብረት ስራ ማህበራት እና 10 የሸማች ዩኒየኞች ዝግጁ ናቸው ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ክልል የሚገኙ የግብርና ምርት አምራች ሕብረት ስራ ዩኒየኖች የግብርና ምርቶችን በማቅረብ ረገድ በጥምረት እንደሚሰሩ የተገለፀ ሲሆን፥ አስፈላጊ የሆኑ የኢንዱስትሪ ምርቶችን ደግሞ ከአምራች ኢንዱስትሪዎች ጋር በቀጥታ የገበያ ትስስር በመፍጠር ምርቶች ወደ ከተማዋ እንዲገቡ ይደረጋል ነው ያሉት።፡
በማህበራቱ በኩል ወደ ከተማዋ እየገቡ ከሚገኙ ምርቶች መካከል፥ እንደ ዶሮ እንቁላል እንዲሁም እንደ በሬ፣ በግ፤ ፍየል ያሉ የቁም እንስሳትና የእንስሳት ተዋፅዖ ውጤቶች እንዲሁም ሽንኩርትን ጨምሮ የፍጆታ ሸቀጦች እየቀረቡ ነው።
የሕብረት ሸማች ማሕበራት በዓልን ተከትለው ሳይሆን ዓመቱን ሙሉ ገበያን በማረጋጋት ስራ ላይ መሆናቸውን ጠቅሰው ÷ በበዓላት ጊዜ ግን የተለየ ፍላጎት ከሕብረተስቡ ስለሚቀርብ ፍላጎት ለማሟላት ከገበያው በተለየ ሁኔታ ምርቶች ይቀርባሉ ብለዋል።
እንደ ዱቄት ያሉ የድጎማ ምርቶችም ለሕብረተሰቡ እየቀረቡ መሆኑንም ገልጸዋል።
በሲሳይ ጌትነት