Fana: At a Speed of Life!

ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ስራውን ለመጀመር ዝግጁ መሆኑን ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 26፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ከመንግስት ጋር ስምምነት በገባው መሰረት ስራውን ለመጀመር ቁርጠኛ መሆኑን አስታወቀ።

ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ እስከዛሬ ባከናወናቸው ተግባራትና በቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ከገንዘብ ሚኒስቴር የስራ ሃላፊዎች ጋር ተወያይቷል።

የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ኩባንያ ዋና ስራ አስፈፃሚ ፒተር ንዴግዋ ኩባንያቸው በውል ስምምነቱ መሰረት ከፈረንጆቹ 2022 ጀምሮ ሥራውን ለመጀመር ያለውን ቁርጠኝነት ገልጸዋል።

ዋና ሥራ አስፈፃሚው ኩባንያቸው ዕቅዱን ከግብ ለማድረስ ያከናወናቸውን በርካታ ሥራዎች ገልፀው÷ አገልግሎት በፍጥነት ለመጀመር ያስችላቸው ዘንድም ከሀገር በቀል ድርጅቶች እና ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በትብብር እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሺዴ በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግስት በቴሌኮሙዩኒኬሽን ዘርፍ ጥራት፣ ተደራሽነት እና ፈጠራ የታከለበት የአቅርቦት እና የማሻሻያ ስራዎችን እንደሚያበረታታ ተናግረዋል።

አያይዘውም ለኩባንያው አስፈላጊውን ትብብርና ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

ከዚህ ባለፈም መንግሥት በሀገሪቱ የተጀመረውን የቴሌኮሙዩኒኬሽን ኢንቨስትመንት ዘርፍ መነቃቃት በቀጣይነት እንደሚደግፍም አውስተዋል።

በቀጣይም ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች ቀጥተኛ እና ቀጥተኛ ያልሆኑ ሥራዎችን እንደሚፈጥር ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

 

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
                                                                                       ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.