“የኛ ሆም” የተሰኘ ልዩ አገልግሎት ሰጪ መተግበሪያ ይፋ ሆነ
አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 25 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) “የኛ ሆም” የተሰኘ አገልግሎት ሰጪና ፈላጊዎችን የሚያገናኝ የኢንተርኔት ቴክኖሎጂ መተግበሪያ ይፋ ሆነ።
ቴክኖሎጂው የውጪ ሀገርና የሀገር ውስጥ እንግዶች ከአገልግሎት ሰጪ ሆቴሎች፣ ልዩ የእንግዳ ማረፊያዎች፣ የግለሰብ ቤቶች፣ ሆስቴሎችና ሪዞርቶች በቀላሉ የሚያገናኝ ነው።
አገልግሎቱ የድረ ገጽ መጠቀሚያ (ዌብሳይት)፣ የሞባይል መተግበሪያ እና የጥሪ ማዕከል መገልገያዎችን በመጠቀም አገልግሎት ሰጪን ከአገልግሎት ፈላጊ ያገናኛል፡፡
የፕላን ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ እንዳልካቸው ስሜ የአስር ዓመቱ የሀገሪቱ የልማት ዕቅድ ላይ የግሉ ሴከተር፣ የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ትልቅ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።
በአስር አመቱ የሀገሪቱ የልማት መሪ ዕቅድ ላይ ለቱሪዝምና የግሉ ዘርፍ መሪ የሆነበት ኢኮኖሚ መፍጠር መታቀዱን የገለፁት ምክትል ኮሚሽነሩ፥ እንደ “የእኛ ሆም” ያሉ የቴክኖሎጂ አገልግሎቶች ለዚህ አስተዋዕጾ ያደርጋሉ ብለዋል፡፡
በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የአይሲተ ዘርፍ ዳይሬክተር ጀነራል ዶክተር አብዮት ሲናሞ”የእኛ ሆም” የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ራዕይ ለማሳካት አስተዋፅኦ የሚያበረክት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
እንዲህ ያሉ የቴክኖሎጂ አገልግሎቶች ባለንበት ቦታ የፈለግነውን አገልግሎት ለማግኘት አስተዋፅኦዋቸው የጎላ መሆኑን ያብራሩት ዳይሬክተር ጀነራሉ፥ አገልግሎቱን የሚጠቀም ማህበረሰብ ለመፍጠር የዲጂታል እውቀት መፍጠር ላይ እየተሰራ ነው ብለዋል።
የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ ካስቀመጣቸው መሪ አቅጣጫዎች አንዱና ዋናው ቱሪዝምን በቴክኖሎጂ ማገዝ በመሆኑ እንዲህ ያሉ ቴክኖሎጂዎች ለዘርፉ መነቃቃት የጎላ አስተዋፅኦ እንዳላቸው ተናግረዋል።
የእኛ ሆም መስራች አቶ ዮሐንስ ተድላ ቴክኖሎጂው አገልግሎት ፈላጊውንና ሰጪውን በቀላሉ ከማገናኘት በዘለለ በሀገር የቀል ቴክኖሎጂዎችን ጥቅም ላይ በማዋል የውጭ ምንዛሬ ወጪን ለማስቀረት ይረዳል ብለዋል።
አሁን ሆቴልና እንግዳ ማረፊያ ማግኘት እንዲሚያስቸግርና የውጭ ፕላትፎርሞችን በውጭ ምንዛሪ እንደሚጠቀም በመጠቆም የኛ ሆም ይህን እንደሚቀርፍና ሀገር በቀል አገልግሎት ሰጪ በመጠቀም ሀብት ሀገር ውስጥ እንዲቀር የሚያደርግ መሆኑን ገልጿል፡፡
ዛሬ በይፋ የተመረቀው የድረ ገጽ መጠቀሚያ (ዌብሳይት) ሲሆን ቀሪዎቹ የሞባይል መተግበሪያ እና የጥሪ ማዕከል አገልግሎቶች በቀጣይ አገልግሎት ላይ እንደሚውሉ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!