የፓዊ ወረዳ የህልውና ዘመቻውን የሚቀላቀሉ ሚሊሻ እና ተጠባባቂ ሃይሎችን አስመረቀ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 18፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በመተከል ዞን የፓዊ ወረዳ የህልውና ዘመቻውን የሚቀላቀሉ ሚሊሻ እና ተጠባባቂ ሃይሎችን አሰልጥኖ ማስመረቁን የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ አሰፋ ገለጹ፡፡
ወረዳው የስነ-ልቦና ዝግጅት እና ተግባር ተኮር ስልጠና በመስጠት እስከ ግንባር ድረስ ዘልቆ ጠላትን ሊደመስስ የሚችል ጠንካራ ሃይል ማዘጋጀቱን አብራርተዋል፡፡
የአካባቢውን ጸጥታ እና ደህንነት በትኩረት በመከታተል ሀገር አፍራሹን የጁንታ ተላላኪ ለመደምሰስ የወረዳው ህዝብ በዝግጅት ላይ መሆኑን ነው አቶ ብርሃኑ የገለጹት፡፡
በአካባቢው ከሚገኝ የመከላከያ ሰራዊት ጋር በቅንጅት በመስራት ዘላቂ የሰላም እና የጸጥታ ደህንነትን ማረጋገጥ እንደሚቻልም ጠቁመዋል፡፡
በአካባቢው የሚገኘው ክፍለ ጦር ምክትል አዛዥ ኮሎኔል መልካሙ በየነ÷ ከጫፍ እስከ ጫፍ በህብር የምንኖርባት አንድ ሀገራችን ለማስከበር አሁናዊ ተልዕኮ ተቀብላችሁ በጠንካራ ሞራል ሰልጥናችሁ ጠላትን ለመደምሰስ በመዘጋጀታችሁ እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል፡፡
እስከ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ድረስ በመዝለቅ የሠላም ደህንነቱን ከመከላከያ ሰራዊት ጋር በመቀናጀት ማረጋገጥ የሚችል ጠንካራ አደረጃጀት እንደተፈጠረ መናገራቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ተመራቂዎችም ሀገራዊ ዘመቻውን መቀላቀላቸው እንዳስደሰታቸው ገልጸው ÷በተሰጣቸው ስልጠና መሰረት ከመከላከያ ጋር በመሆን ጠላትን ለመደምሰስ ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል ፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!