Fana: At a Speed of Life!

ኤጀንሲው የሳይበር ደህንነት ስጋት በሁሉም ተቋማት ላይ መኖሩን ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 17፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ በ2013 ዓ.ም ባደረገው የሳይበር ደህንነት ፍተሻ 60 በሚሆኑ ተቋማት ላይ የተፈጠሩ የሳይበር ጥቃት ተጋላጭነቶችን መለየት መቻሉን እና ክፍተቶቹም እንዲታረሙ ማድረጉን ገለጸ፡፡

በኤጀንሲዉ የሳይበር ደህንነት ፍተሻ እና ግምገማ ዲቪዥን ሀላፊ አቶ ደሳለኝ ወልደጊዮርጊስ እንደገለጹት በተጠናቀቀው 2013 በጀት አመት ኤጀንሲው በ60 የመንግስት እና የግል ተቋማት ላይ ጥልቅ የደህንነት ፍተሻዎችን ያደረገ ሲሆን ተቋማቱ ከከፍተኛ እስከ ዝቅተኛ ደረጃ ለሳይበር ጥቃት ተጋላጭ እንደነበሩ አብራርተዋል፡፡

የሳይበር ደህንነት ፍተሻ የተደረገላቸው ሁሉም ተቋማት የሲስተም፣ የሳይበር መሰረተ-ልማት ፣ የሰው ሃይል እና የሳይበር ደህንነት አስተዳደር ክፍተት እንደተገኘባቸውም ነው የተገለፀው፡፡

ከተለዩት የሳይበር የደህንነት ክፍተቶች መካከል 84.5 በመቶ የሚሆኑት ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርሱ ሲሆን 8 ነጥብ 9 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ በመካከለኛ ደረጃ እንዲሁም 6 ነጥብ 6 በመቶዎቹ ጉዳታቸው ዝቅተኛ የሚባሉ ክፍተቶች እንደነበሩ ሃላፊው ጠቁመዋል፡፡

እነዚህን የሳይበር ጥቃት ተጋላጭነቶችን ለመቅረፍም ተቋማቱ በኤጀንሲዉ የተሰጣቸውን ምክረ ሃሳብ መሰረት በማድረግ ክፍተቶቹን ማስተካከል፣ ማንኛውም ሲስተም ወይም የሳይበር መሰረተ-ልማት ከመተግበሩ በፊት የደህንነት ፍተሻ እንዲደረግለት ማድረግ፣ ተቋማቱ በሳይበር ደህንነት ዙሪያ የሰራተኞቻቸውን ንቃተ ህሊና ማሳደግ ይኖርባቸዋል ማለታቸውን ከኤጀንሲው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.