አንጋፋው የጥበብ ሰው መሐመድ አወል ሙሐመድ ሳላህ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 17፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በበርካታ የጥበብ ስራዎቹ የሚታወቀው የጥበብ ሰው መሐመድ አወል ሳላህ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ።
መሐመድ አወል ባደረበት የልብ ህመም ምክንያት በትናንትናው እለት ነው ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው።
መሐመድ አወል ደሴ ከተማ አራዳ አካባቢ ከእናቱ ከወይዘሮ ሰዕዲያ ሰዒድ አህመድ እና ከአባቱ ሐጅ ሙሐመድ ሳላህ አህመድ በ1958 የተወለደ ሲሆን፥ በወይዘሮ ስህን ትምህርት ቤት ትምህርትን ተከታትሏል።
ከትምህርት በኋላም ወደ ውትድርናው ዓለም በመቀላቀል ሃገሩን ሲያገለግል ቆይቷል።
በወታደር ቤትም በሙዚቀኝነት ሲያገለግል ቆይቶ ወደ ሳዑዲ አረቢያ በማቅናት ለሰባት ዓመታት ቆይታ አድርጎ ወደ ሃገሩ በመመለስ የጥበብ ስራውን ሲሰራ ቆይቷል።
ከዓለማዊው የሙዚቃ ዓለም በኋላም ወደ መንፈሳዊ ህይወት በማዘንበሉ ህይወቱ እስካለፈችበት እለት ድረስ ሙሉ በሙሉ ኢስላማዊ የኪነጥበብብ ሲያገለግል ቆይቷል።
መሐመድ አወል በሙዚቃው ዓለም ከሰራቸው ስራዎች ባሻገር በእስልምናው ዓለም በርካታ የጥበብ ስራዎችን አበርክቷል።
የለኝ በጎ ሥራ፣ ሙሐመድ ተብዬ፣ እመስገጃሽ ላይ ታገሺ፣ ውዴታ እስከጀነት እና ሌሎችም የተካተቱበት ሶስት አልበሞችንና በርካታ ነጠላ ነሺዳዎችን አበርክቷል።
ከሚታወቅበት የጥበብ ሥራ በላቀ መልኩ የበጎ ተግባራት ላይ ከፍተኛ ተሳትፎ እንዳለው የቅርብ ወዳጆቹ ይመሰክራሉ።
ባለትዳር እና የስድስት ልጆች አባት የሆነው ሙንሺድ መሐመድ አወል ሳላህ ለረጅም ግዜ የዘለቀ ልብ ታማሚ የነበረ ሲሆን በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ህክምናውን ሲከታተል ቆይቶ በትናንትናው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።
የቀብር ስነ ስርዓቱም ኮልፌ በሚገኘው የሙስሊም መካነ መቃብር ዛሬ ከቀኑ 7 ሰዓት ላይ ይፈጸማል።
ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ለመላው ቤተሰቦቹ፣ ወዳጆቹና ለመላው ኢትዮጵያውያን የጥበብ አፍቃሪዎች መጽናናትን ይመኛል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!