“እኔም ለሀገሬ ወታደር ነኝ” በሚል የመከላከያ ሠራዊትን የሚደግፍ ሩጫ በሶዶ ከተማ ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 15፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) እኔም ለሀገሬ ወታደር ነኝ በሚል ርዕስ የሀገር መከላከያ ሠራዊትን የሚደግፍ ሩጫ በወላይታ ዞን ሶዶ ከተማ ተካሄደ።
የደቡብ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ብሩ ቡናሮ፥ የሩጫው ዋና አላማ ሀገራችን ከውጭ በኃያላን ሀገራት ከውስጥ ደግሞ በከሀዲዎች ኢትዮጵያ እየደረሰባት ያለውን ጫና መቃወምና የአባቶቻችን ገድል ለመድገም ዳር ድንበሯን ለማስከበር የዘመተውን የሀገር መከላከያ ሠራዊት ለመደገፍ መሆኑን አስረድተዋል።
አያይዘውም በሁሉም የክልል ከተሞች መሰል ድጋፍ እንደሚቀጥል ጠቅሰው፥ የሀገርን ሰላም የሚያስከብሩ ቆራጥ ዜጎች በመኖራቸው ኩራት እንደተሰማቸው ነው የገለፁት።
የወላይታ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የትራንስፖርትና መንገድ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ፎላ በበኩላቸው፥ የዞኑ ህዝብ የሀገር ህልውና ለመጠበቅ በየትኛውም አቅጣጫ ዝግጁ መሆኑን ገልፀው ለኃያላን ሀገራት ፍርደ ገምድል ዳኝነታቸው እጅ አይሰጥም ብለዋል።
ራሳቸውን የዴሞክራሲ አባት አድርገው የሚያዩት ያደጉ ሀገራት የኢኮኖሚ ጫና በማሳደር ከሽብርተኛው ቡድን ጋር እንድንደራደር የአዞ እምባ ያነባሉ ያሉት አቶ ሳሙኤል የኃያላኑ ሀገራት ዋና አላማ እንደፈለጉት የምትጠማዘዝ ደካማ ኢትዮጵያን መፍጠር አስረድተዋል።
የአምስት ኪሎሜትር ሩጫውን ጨምሮ የእግር ኳስና የወርልድ ቴኳንዶ ውድድር እንዲሁም የተለያዩ ስፖርታዊ ክንውኖች ለሀገር መከላከያ ድጋፍ ለማሰባሰብ ይደረጋል።
በመለሰ ታደለ