የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር የኢኮኖሚ አሻጥር በሚፈጥሩ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ እንደሚወስድ አስታወቀ
አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 15 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢኮኖሚ አሻጥር በሚፈጥሩ ነጋዴዎች ላይ የማያዳግም እርምጃ እንደሚወሰድ የባህርዳር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳህሉ ገለጹ።
ወቅታዊ ሁኔታውን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም በምርቶች ላይ የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ በመንግስት ላይ ጫና ለመፍጠር ጥረት የሚያደርጉ ነጋዴዎች መኖራቸውን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፓሬት ተናግረዋል።
በእንደዚህ አይነት ጊዜ በጋራ በመቆም ለወገን ማሰብ ሲገባ የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ ማህበረሰብን ማማረር ከጠላት ጋር እንደመተባበር ይቆጠራል ያሉት ዶክተር ድረስ ሳህሉ መንግስት ይህን ተግባር አይታገስም ብለዋል።
ችግሩን ለመፍታት ግብረሀይል ተቋቁሞ ወደስራ የተገባ ሲሆን በቁጥጥር ስራው የሚገኘውን ውጤት መሰረት አድርጎ በተግባሩ ተሳትፈው በተገኙ አካላት ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ ይወዳል ነው ያለው ከተማ አስተዳደሩ።
በህወጥ ተግባር የሚሳተፉ አካላትን የከተማው ማህበረሰብ በመጠቆም የበኩሉን ሀላፊነት እንዲወጣ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ጥሪ አቅርበዋል።
በምናለ አየነው