በአዲስ አበባ በረዶ የቀላቀለ ከባድ ዝናብ በሕይወት እና ንብረት ላይ ጉዳት አደረሰ
አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 11 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በመዲናዋ የጎርፍ አደጋ ተከስቶ በሰው ሕይወት እና ንብረት ላይ በደረሰው ጉዳት ከልቤ አዝኛለሁ ሲሉ የአዲሰ አበባ ከተማ አስተዳደር ም/ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ መልዕክት አስተላለፉ።
ከክረምቱ እየጠነከረ መምጣት ጋር ተያይዞ ዛሬ ከሰዓት በኋላ በመዲናችን አዲስአበባ በጣለው በረዶ የቀላቀለ ከባድ ዝናብ ምክንያት በተለያዩ የከተማችን አካባቢዎች የጎርፍ አደጋ ተከስቶ በሰው ሕይወት እና ንብረት ላይ በደረሰው ጉዳት ከልቤ አዝኛለሁ ነው ያሉት ምክትል ከንቲባዋ።
በአስኮ፣ በአደይአበባ፣ በጀርመን አደባባይና በጎልፍ ክለብ አካባቢ በደረሰው ከፍተኛ የጎርፍ አደጋ እስከአሁን ድረስ መንገዶች ጭምር የተዘጋጉ ሲሆን፣የድንገተኛና የእሳት አደጋ ሰራተኞቻችን በቦታዎቹ በመገኘት የከፋ ሰብዓዊ ጉዳት እንዳይደርስ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው።
ተጎጂዎችንም ወደ ህክምና መስጫ በማጓጓዝ እና የመጀመሪያ ህክምና እርዳታ በማድረግ ላይ እንገኛለን ብለዋል።
የከተማው አስተዳደር ከክረምቱ ማየል ጋር ተያይዞ አስቀድሞ የመከላከል ስራዎችን እየሰራ የነበረ ቢሆንም የዛሬው አደጋ ተጨማሪ ስራዎችን መስራት እንደሚገባ ያመላከተ ነዉ።
አሁንም መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በመጪዎቹ ቀናት ከፍተኛ መጠን ያለዉ የዝናብ ስርጭት ስለሚኖር ነዋሪዎች አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንድታደርጉ አደራ እላለሁ ሲሉ ወ/ሮ አዳነች በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው መልዕክት አሰተላልፈዋል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!