በቶኪዮ የፓራኦሊምፒክ ጨዋታዎች ተመልካቾች በስቴዲየም አይታደሙም
አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 10፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በጃፓን ቶኪዮ የፓራ ኦሊምፒክ ጨዋታዎች ያለ ተመልካች እንደሚካሄዱ አስተባባሪዎች አስታወቁ።
ከኮሮና ቫይረስ ስርጭት መጨመር ጋር ተያይዞ ቫይረሱን ለመቆጣጠር ጃፓን ከፍተኛ ችግር ውስጥ በመውደቋ ተመልካቾች ጨዋታዎችን በአካል ተገኝተው አይታደሙም ተብሏል።
የጨዋታዎቹ አስተባባሪዎች ደጋፊዎች በየጎዳናው ጨዋታዎችን ተሰባስበው እንዳይመለከቱም መጠየቃቸው ተሰምቷል፡፡
የቫይረሱ ስርጭት በተለይ በቶኪዮ፣ ሳኢታማ፣ ቺባ እና ሺዙኦካ ከፍተኛ በመሆኑ ተመልካቾች ማናቸውንም አይነት የድጋፍ ትዕይንቶች ማካሄድ እንደማይችሉ ነው የተገለፀው፡፡
ከቫይረሱ ስርጭት መጨመር ጋር ተያይዞ የሀገሪቷ መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማራዘም ሀሳብ ማቅረቡም እየተነገረ ነው፡፡
የፓራኦሊምፒክ ጨዋታዎች ነሐሴ 24 ቀን እንደሚጀመሩ ቢቢሲ በዘገባው አመላክቷል።