አሜሪካና ኢራቅ ባግዳድ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት አወገዙ
አዲስ አበባ፣ጥር 19፣2012 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካ እና ኢራቅ ሰሞኑን ባግዳድ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ላይ የተፈጸመውን የሮኬት ጥቃት አውግዘዋል።
የኢራቅ ጠቅላይ ሚኒስትር አዴል አብዱል መሃዲ እና የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ በጉዳዩ ዙሪያ ተወያይተዋል።
በውይይታቸውም በሀገራቱ መካከል ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማጠናከር እንዲሁም ባግዳድ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን መከላከል በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።
በኤምባሲው ላይ የሮኬት ጥቃት የፈጸመውን አካል ተገቢ ምርመራ በማካሄድ ለህግ ለማቅረብ በቅንጅት የሚሰሩ መሆኑንም አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አዴል አብዱል መሃዲ የኢራቅን ሉዓላዊነት በመጣስ በሀገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ላይ አላስፈላጊ ጣልቃ ገብነት የሚፈፅሙ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።
ማይክ ፖምፒዮ በበኩላቸው የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ከማስጠበቅ አንጻር ሀገራቸው ቁርጠኛ መሆኗን ተናግረዋል።
ለዚህም በጉዳዩ ዙሪያ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በየትኛውም ጊዜ ለመወያየት ዝግጁ መሆናቸውን ነው ያረጋገጡት።
ባሳለፍነው ዕሁድ ዕለት ባግዳድ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ላይ በትንሹ ሦስት የሮኬት ጥቃቶች መፈጸማቸው ይታወቃል።
በተፈጸመው ጥቃት ሶስት ሰዎች የቆሰሉ ሲሆን፥ ለጥቃቱ እስካሁን ሃላፊነት የወሰደ አካል አለመኖሩ በዘገባው ተመላክቷል።
ምንጭ፦ሺንዋ