በዩጋንዳ የቡጎማ ደን መመናመን ያሳሰባቸው ተቆርቋሪዎች ደኑን ለመጠበቅ ቁርጠኛ መሆናቸውን ገለጹ
አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 2፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በዩጋንዳ የቡጎማን ደን መመናመን ያሳሰባቸው ተቆርቋሪዎች ደኑን ለመጠበቅ ቁርጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ከፈረንጆቹ ነሐሴ 2020 ጀምሮ ከዩጋንዳ ከተማ በስተሰሜን ምዕራብ በኩል 250 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የቡጎማ ደን ለስኳር አገዳ ልማት በሚል ምክንያት ነበር በግሬደር መታረስ የጀመረው፡፡
የአካባቢው ነዋሪዎችና የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች በድርጊቱ በመቆጣት`የቡጎማን ደን እናድን` በሚል መሪ ቃል ተቃውሟቸውን ለማሰማት መሰባሰባቸው ይታወሳል፡፡
በወቅቱ ነዋሪዎቹ እንደተናገሩት የደኑን መመንጠር ተከትሎ ዝንጀሮዎችና የዱር እንስሳት በመኖሪያ አካባቢዎቻቸው እየሄዱ ጉዳት ከማድረሳቸውም ባሻገር ሰብላቸውንም እያወደሙ ነው፡፡
በአካባቢው የተፈጠረውን ተቃውሞ ተከትሎ ፖሊሶችና የጥበቃ ሰራተኞች በንሶዚ መንደር አቅራቢያ መስፈራቸውን አልጀዚራ በዘገባው አስታውሷል፡፡
የአካባቢ ጥበቃ ተከራካሪዎቹ በፈረንጆቹ ግንቦት ወር በመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ክስ ቢመሰርቱም፣ እውነታውን ደብቃችሁ፤ ደኑ ሙሉ በሙሉ እንደተጨፈጨፈ አድርጋችሁ በማጋነን አቅርባችኋል በሚል ውድቅ እንደተደረገባቸው ተገልጿል፡፡
አሁን ላይ የአካባቢ ጥበቃ ተከራካሪዎቹ ጉዳዩን ወደ ሀገሪቷ ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንደወሰዱትም ነው የታወቀው፡፡
ከፍተኛው ፍርድ ቤት ከአንድ በላይ በሆኑ ዳኞች ስለሚመራ ጉዳያችን እዚያ መፍትሄ ያገኛል የሚል እምነትም እንዳላቸው ነው ተስፋ ያደረጉት፡፡
የቡጎማ ደን 400 እስኩዌር ኪ.ሜ የሚሸፍን ሲሆን÷ ከዩጋንዳ ዋና ከተማ በ250 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሰሜን ምዕራብ ክፍል ይገኛል፡፡
በደኑም 38 ዓይነት የአጥቢ እንስሳት ዝርያዎች ሲገኙ ÷ አራቱ በዓለማችን ላይ በመጥፋት ላይ የሚገኙ እንደሆኑና ዘጠኙ ደግሞ ከፍተኛ ጥበቃ እንዲደረግላቸው በዓለም አቀፍ የተፈጥሮ ጥበቃ የተመዘገቡ መሆናቸው ነው የታወቀው፡፡
በደኑ ውስጥ አሁን ባለው ሁኔታ 600 የሚሆኑት የዝንጀሮ ዝርያዎች እንዳይመናመኑ ተሰግቷል፡፡
ምንጭ÷አልጀዚራ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!