የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በስድስት ወራት ውስጥ የጎብኚዎች ፍሰት መጨመሩን ገለፀ
አዲስ አበባ፣ ጥር 16፣ 2012(ኤፍ.ቢ.ሲ) የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በበጀት አመቱ 6 ወራት የክልሉ የጎብኚዎች ፍሰትና ገቢ መጨመሩን አስታወቀ።
ቢሮው በ2012 በጀት ዓመት የመጀመሪያ 6 ወራት 8 ሚሊየን 176 ሺህ 623 የሀገር ውስጥ ጎብኚዎችን ለመሳብ አቅዶ 7 ሚሊየን 26 ሺህ 662 ጎብኚዎች ክልሉን መጎብኘታቸውን ገልጿል።
የባህልና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም ምርትና አገልግሎት ልማት ባለሙያ አቶ ጥላሁን መዝገቡ ቁጥሩ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ1 ነጥብ 8 ሚሊየን ብልጫ እንዳለው ተናግረዋል።
በተመሳሳይ 225 ሺህ 220 የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ክልሉን ለማስጎብኘት ታቅዶ 105 ሺህ 313 መጎብኘታቸውን እና ይህ ቁጥር ካለፈው አመት በ9 ሺህ ጎብኚዎች ጭማሪ ማሳየቱን ባለሙያው አንስተዋል።
ከላይ ከተጠቀሰው የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎች 1 ቢሊየን 792 ሚሊየን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 1 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር መገኘቱንም ነው አቶ ጥላሁን የገለፁት።
ይህም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ177 ሚሊየን ብር ብልጫ እንዳለው አስረድተዋል።
በክልሉና በሀገሪቱ አሁን ላይ አንጻራዊ ሠላም መታየቱ ለክልሉ የቱሪዝም ፍሰትና ገቢ መጨመር ምክንያት መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ሀገሪቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ማዕከል (ዩኔስኮ) ያስመዘገበቻቸው ቅርሶች መጨመርና በሚዲያዎች የማስተዋወቅ ስራ መሰራቱ ለጭማሪው ሌላው ምክንያት መሆኑንም አብራርተዋል።
ከዚህ ባለፈም የክልሉ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም መዳረሻዎችን የማብዛት፣ የመለየትና የመረጃ አያያዝ ማደግም ለጎብኚዎች ፍሰትና ገቢ መሻሻል ጉልህ ድርሻ አድርጓል ብለዋል።
በናትናኤል ጥጋቡ