በቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ለመሳተፍ ከምንጊዜውም በላይ ዝግጅት መደረጉ ተገለፀ
አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 24 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)በጃፓን ቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ለመሳተፍ ከምንጊዜውም በላይ ዝግጅት መደረጉን ተገለፀ።
ዝግጅቱን በማስመልከት የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ እና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ በሂልተን ሆቴን በጋራ መግለጫ ተሰጥተዋል።
የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ጨዋታ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተከሰተው የኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ለአንድ ዓመት መራዘሙ ይታወቃል።
ውድድሩ በፈረንጆቹ ከሀምሌ 23 እስከ ነሀሴ 8 ቀን 2021 የሚካሄድ ሲሆን ከ206 ሀገራት የተውጣጡ ከ11 ሺህ በላይ ስፖርተኞች ይሳተፋበታል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተገልጿል።
ኢትዮጵያም በዚህ ወድድር ለመሳተፍ እና የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ከመቼውም ጊዜ በላይ ዝግጅት መደረጉን የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ ገልፀዋል።
ዶከተር አሸብር በቶኪዮ ኦሊምፒክ የሚደደረገው ተሳትፎ የተለየ የሚያደርገው ሻምበል አበበ ቢቂላ ኦፕሬሽን ሆኖ ያሸነፈበትን ድል የምንዘክርበት እና ዳግም ድል በማስመዝገብ የሀገራችንን ሰንደቅ አላማ ከፍ ለማድረግ ዝግጅት የተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።
ይህን ለማሳካትም አትሌቶች ከ8 ወር በላይ ሆቴል ውስጥ ሆነው ዝግጅት ሲያደርጉ ቆይተዋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ በበኩላቸው ÷ በዘንድሮው ኦሊምፒክ ለመሳተፍ በሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጭ በተካሄዱ የውድድር ውጤቶችን መሠረት በማድረግ በስድስት የአትሌቲክስ ውድድር ዲሲፕሊኖች 34 አትሌቶች ተመልምለው ለኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ማቅረባቸውን ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን እና የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንቶች በቶኪዮ ኦሊምፒክ ለመሳተፍ እያደረጉት ያለውን ዝግጅት በመግለጫው አብራርተዋል።
በቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ ፣ በወርልድ ቴኳንዶ ፣ በብስክሌት እና በውሃ ዋና በአራት እንደምትሳተፍ የስፖርት ዓይነቶች ከኢትዮጵያ ስፖርት ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!