ባለፉት ስድስት ወራት ከ1 ቢሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች ተያዙ
አዲስ አበባ ፣ ጥር 15 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ባለፉት ስድስት ወራት ከ1 ቢሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎች መያዙን የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን አስታወቀ።
ኮሚሽነሩ አቶ ደበሌ ቃበታ እንደገለጹት ዕቃዎቹ የተያዙት በሃገሪቱ ወጪና ገቢ ዕቃዎች ላይ በተካሄደ ጸረ ኮንትሮባንድ ቁጥጥር ነው።
ከተያዙት እቃዎች መካከል ልባሽ ጨርቅ፣ አዳዲስ አልባሳት እና የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዙ ኮሚሽነሩ ገልፀዋል፡፡
ጊዜ ያለፈበት መድኃኒት፣ አደንዛዥ ዕጾች፣ የመለዋወጫ እቃዎች፣ የምግብ ሸቀጣ ሸቀጦች እና ሌሎች ቁሳቁሶች ከተያዙት መካከል ይጠቀሳሉ።
በአየር መንገድ በተደረገ ቁጥጥር የውጭ ገንዘብ መያዙንም ተናግረዋል።
በተጨማሪም በሰሜን ምዕራብ የሃገሪቱ ክፍሎችና በሌሎችም አካባቢዎች ሲጓዙ የነበሩ የጦር መሣሪያዎች መያዛቸውን አንስተዋል።
ከችግሩ ግዝፈት አንፃር ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት፣ ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከክልል የጸጥታና ከሌሎችም አካላት ጋር በቅንጅት መሰራቱንም አመልክተዋል።
እንዲሁም ከሃገር ሊወጡ የነበሩ 230 ሚሊየን ብር ግምት ያላቸው የማዕድን ምርቶችና የቁም እንስሳት ድንበር ላይ መያዛቸውንም አስረድተዋል።
በሥራው ካለፈው ዓመት የተሻለ ውጤት ቢመዘገብም፤ አሁንም እንቅስቃሴው ፈታኝ ሆኖ መቀጠሉን ያነሱት ኮሚሽነሩ÷ በቀጣይ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት እንደሚሰራ መግለፃቸውን ከኢዜአ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።