Fana: At a Speed of Life!

በምርጫው ኢትዮጵያን አሸናፊ ማድረግ ተችሏል-ብልጽግና ፓርቲ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 16፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በማካሄድ አሸንፋለች ሲል የብልጽግና ፓርቲ አስታውቋል።
የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ዛሬ አስቸኳይ ስብሰባ አካሄዷል።

የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት ኃላፊና ሥራ አስፈጻሚ አባል አቶ ብናልፍ አንዷለም ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በዛሬ ስብሰባው ፓርቲው በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ያከናወናቸውን ተግባራት ገምግሟል።

ፓርቲው ወደ ምርጫው ሲገባ ሁለት ዋነኛ ዓላማዎችን ለማሳካት አቅዶ መንቀሳቀሱን ጠቅሰው፤ ቀዳሚ ዓላማው ያደረገው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በማካሄድ ኢትዮጵያን አሸናፊ ለማድረግ የበኩሉን ሚና መጫወት መሆኑን ገልጸዋል።

በምርጫው አሸናፊ ሆኖ ከህዝብ የመንግስት ኃላፊነት መቀበል ደግሞ ሌላኛው ዓላማ መሆኑን ተናግረዋል።

ስራ አስፈጻሚው በዛሬው የፓርቲው ስብሰባ በዋናነት በምርጫው ኢትዮጵያን አሸናፊ ማድረግ የሚለውን የፓርቲውን ቀዳሚ ዓላማ ለማሳካት የተከናወኑ ተግባራትን ገምግሟል ብለዋል።

ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በማካሄድ በምርጫው ኢትዮጵያን አሸናፊ ማድረግ እንደተቻለ መገምገሙን ተናግረዋል።

ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው “በምርጫው አሸናፊ ሆኖ ከህዝብ የመንግስት ኃላፊነት መቀበል” የሚለውን የፓርቲውን ሁለተኛ አንኳር ዓላማ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ የምርጫውን ውጤት ይፋ ካደረገ በኋላ እንደሚገመግመው ገልጸዋል።

ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ደግሞ ኢትዮጵያውያን አይተኬ ሚና መጫወታቸውን ነው ያነሱት።

በዚህም የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ለመላው ኢትዮጵያውያን ምስጋና አቅርቧል ብለዋል።

ያለ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ትብብር ምርጫውን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ማከናወን አይቻልም ነበር ያሉት ኃላፊው፤ በመሆኑም ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በምርጫው የተሳተፉ ፓርቲዋች ለሂደቱ ሰላማዊነት ላደረጉት አስተዋጽኦ ምስጋና ማቅረቡን አስታውቀዋል።

ምርጫ ቦርድ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተቋማዊ አደረጃጀቱን አስተካክሎ ምርጫውን ለማከናወን የሄደበትን ርቀትም አድንቀዋል።

የመገናኛ ብዙሃን የምርጫውን ሂደት ለህዝብ ተደራሽ በማድረግ ረገድ ጉልህ ስራ እንዳከናውኑም ስራ አስፈጻሚው መገምገሙን ያወሱት አቶ ብናልፍ፤ ለዚህም አድናቆቱን መግለጹን ተናግረዋል።

በቀጣይ በሌሎች አከባቢዎች የሚካሄደውን ምርጫ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ሁሉም ባለድርሻ አከላት በተለመደው መልኩ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.