ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የመማር ማስተማር ስራውን አውከዋል ባላቸው 21 ተማሪዎች ላይ እርምጃ ወሰደ
አዲስ አበባ፣ጥር 14፣ 2012(ኤፍ.ቢ.ሲ) ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የመማር ማስተማር ስራውን በማወክ በተለዩና ተጨባጭ ማስረጃ በተገኘባቸው 21 ተማሪዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን አስታወቀ።
በዩኒቨርሲቲው አንዳንድ የትምህርት ክፍሎች ተቋርጦ የነበረው ትምህርት ሙሉ በሙሉ መጀመሩም ተገልጿል።
የዩኒቨርሲቲው ኢንፎርሜሽን ስትራቴጂክ ኮሙዩኒኬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ዘውዱ እምሩ፥ አራት ተማሪዎች ሙሉ በሙሉ መታገዳቸውን እና በ21 ተማሪዎች ላይ ደግሞ ከአንድ ዓመት እገዳ ጀምሮ እርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል።
ሌሎች ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ያላቸውን አካላት በመለየትና በማጣራት በቀጣይ ተመሳሳይ እርምጃ እንደሚወሰድም ዩኒቨርሲቲው አስታውቋል።
የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ከመማር ማስተማር ስራው ጎን ለጎን ተማሪዎችን በስነ ምግባር በማነጽ ችግር ፈቺ ሆነው እንዲወጡ ማድረግ እንደሚገባም ዶክተር ዘውዱ ተናግረዋል።
ባለፉት ሳምንታት ተማሪዎች በሚያነሷቸው ጥያቄዎች ዙሪያ ተደጋጋሚ ውይይትና ምክክር ቢደረግም ምክንያታዊ ባልሆነ መንገድ በፖሊ፣ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ፣ ፔዳና ይባብ ግቢዎች ትምህርት ተቋርጦ እንደነበር የኢዜአ ዘገባ ያመላክታል።