ቻይና ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ በሁለት ከተሞች የጉዞ ክልከላ ጣለች
አዲስ አበባ፣ ጥር 14፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ቻይና የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት በማሰብ በሁለት ከተሞች የጉዞ ክልከላ መጣሏ ተሰምቷል።
በሀገሪቱ በተከሰተው እና ለ17 ሰዎች ህልፈት ምክንያት የሆነው የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ይረዳል የተባለው ክልከላ ውሃን እና ሁዋንጋንግ በተባሉ ከተሞች ላይ ነው የተጣለው።
የሀገሪቱ ባለስልጣናት የ11 ሚሊየን ሰዎች መኖሪያ ወደ ሆነችው ውሃን ከተማ አውሮላንም ሆነ ባቡር እንዳይገባና እንዳይወጣ እንዲሁም በከተማዋ ውስጥ ምንም አይነት የየብስ ትራንስፖርት እንቅስቃሴ እንዳይኖር ትዕዛዝ አስተላፈዋል።
7 ሚሊየን ሰዎች በሚኖሩባት ከተማም ተመሳሳይ የጉዞ ክልከላ ከእኩለ ሌሊት ጀምሮ መጣሉን ነው ከስፍራው የወጡ መረጃዎች የሚጠቁሙት።
በሁለቱ ከተሞች ላይ የተጣለው የጉዞ ክልከላ በሚሊየን የሚቆጠሩ ቻይናውያን የሉናር አዲስ ዓመታቸውን ለማክበር በሚንቀሳቀሱበት ወቅት የተጣለ መሆኑም ታውቋል።
በከተሞቹ የጉዞ ክልከላ መጣሉን ተከትሎም የአውሮፕላን ማረፊያዎች እና የባቡር ጣቢያዎች ባዶ መሆናቸው ተነግሯል።
ከዚህ በተጨማሪም በከተሞቹ ካፍቴሪያዎች፣ ሲኒማ ቤቶች እና አውደ ርዕይ የሚካሄድባቸው ስፍራዎች ዝግ መደረጋቸው ነው የተገለፀው።
ሌሎች ከተሞችም የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰዱ ሲሆን፥ ከ1 ሚሊየን በላይ ሰዎች የሚኖሩባት ሁዋንጋንግ ከተማም የባቡር ጣቢያዎቿን መዝጋቷን አስታውቃለች።
በቻይና ዋና ከተማ ቤጂንግም የቻይናውያን ዋና ዋና የአዲስ ዓመት አከባበር ስነ ስርዓቶች ተሰርዘዋል።
የጤና ባለሙያዎችም ሰዎች በሚንቀሳቀሱበት ወቅት የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ በመደበኛነት እንዲያደርጉ እና ሰዎች በብዛት አንድ ቦታ ላይ እንዳይሰበሰቡም እየመከሩ ይገኛል።
በቻይና በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ምክንያት እስካሁን 17 ሰዎች የሞቱ ሲሆን፥ ከ500 በላይ ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ መያዛቸው ነው የተነገረው።
ቻይና ውስጥ የተከሰተው አዲስ ተላላፊ የኮሮና ቫይረስ ወደ ተለያዩ ሃገራት እየተስፋፋ ሲሆን፥ ቫይረሱ አሜሪካን ጨምሮ በታይላንድ እና ደቡብ ኮሪያ መታየቱም ታውቋል።
የመተንፈሻ አካል ችግር፣ ከፍተኛ ትኩሳት፣ መተንፈስ አለመቻል፣ ሳል እና የትንፋሽ መቆራረጥ በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች የሚያሳዩት ምልክት ነው ተብሏል።
ምንጭ፦ ቢቢሲ