የኢትዮጵያ የጤፍ ባለቤትነት መብት ጉዳይ እልባት ሊያገኝ ነው
አዲስ አበባ፣ ጥር 14 ፣ 2012(ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ መድረክ የጤፍ ባለቤትነቷን ለማረጋገጥ የምታደርገው እንቅስቃሴ እልባት ሊያገኝ ነው።
ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ በአንድ ጀርመናዊ ጠበቃ አማካኝነት የተጀመረው የጤፍን የባለቤትነት መብት ለኢትዮጵያ የማስመለስ ሂደት ተስፋ ሰጭ ውጤት ታይቶበታል።
ከዚህ ቀደም አንድ የኔዘርላንድስ ኩባንያ የጤፍ ዱቄትን አገኘሁ በሚል የባለቤትነት መብቱን በማስጠበቅ፥ ጤፍን እሴት ጨምሮ ለአውሮፓ ገበያ በብቸኝነት ሲያቀርብ ቆይቷል።
ይሁን እንጅ ባለፈው አመት ኩባንያው ያቀረበው የባለቤትነት መብት በኔዘርላንድስ ከታየ በኋላ የጤፍ ዱቄት የፈጠራ እና የጤፍ ባለቤትነት መብትን አያስገኝም በሚል ውድቅ መደረጉ ይታወሳል።
ከዚያን ጊዜ ወዲህም ኢትዮጵያ ጉዳዩን ለህግ በማቅረብ የጤፍ ባለቤትነት መብቷ እንዲመለስላት ስትጠይቅ ቆይታለች።
ጀርመናዊው አቃቤ ህግ አንቶን ሆርን በበኩሉ በሙኒክ ከተማ በሚገኝና የባለቤትነት መብትን ጉዳይ ብቻ በሚመለከት ፍርድ ቤት ጉዳዩን ወስዶታል።
ኩባንያው በጀርመናዊ የተከፈተበት የክስ ሂደት ከመጀመሩ አስቀድሞ በጀርመን ያለውን የጤፍ ዱቄት የባለቤትነት መብት በራሱ ጊዜ ሲያነሳ፥ የግለሰቡ የባለቤትነት መብትም በጀርመን ታግዷል።
ይህም ኢትዮጵያ የጤፍ ባለቤትነት መብቷን ሙሉ ለሙሉ ለማስመለስ ለምታደርገው ጥረት ትልቅ ስኬት እና የባለቤትነት መብቱም በቅርቡ እልባት እንደሚያገኝ ማሳያ ነው ተብሏል።
ኩባንያው በተለያዩ የአውሮፓ ሃገራት ያለው የባለቤትነት መብትም በቅርብ ጊዜ ውስጥ ጊዜው የሚያበቃ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የባለቤትነት መብቱን ያጣል ተብሎ ይጠበቃል።
ይህም ጤፍ የማን ነው ለሚለው ጥያቄ ትክክለኛ ምላሽ የሚሰጥና ለኢትዮጵያ የባለቤትነት መብት ማረጋገጫ ለመስጠት መቃረቡን ያመላክታል ተብሏል።
የሆላንዱ ኩባንያ በፈረንጆቹ 2000 መጀመሪያ ከኢትዮጵያ ጋር ጤፍን ለማስተዋወቅና ለገበያ ለማቅረብ ስምምነት ደርሶ ነበር።
ይሁን እንጅ በፈረንጆቹ 2007 ኩባንያው ከስሯል በሚል ሰበብ ኩባንያው እንደተሸጠ በመግለጽ፥ የኩባንያው ገዥዎች የጤፍ ዱቄትን በአውሮፓ ገበያ ብቻቸውን ማቅረብ የሚያስችል የባለቤትነት መብት ከአውሮፓ ህብረት ማግኘታቸው ይታወሳል።
ይህም ከሰብል ምርቶች ባለቤትነትና እሴት ተጨምሮባቸው ለገበያ በሚቀርቡበት ወቅት ባለቤቱ ማግኘት የሚገባውን ጥቅም በመከልከል ዓለም አቀፍ ህግን የጣሰ ነው በሚል ኢትዮጵያውያን ቅሬታቸውን ሲያቀርቡ ቆይተዋል።
የአሁኑ የጀርመን እርምጃም የጤፍን የባለቤትነት መብት ለማስመለስ በተደረገው ጥረት የተገኘ ትልቁ ስኬት ተደርጎ ተወስዷል።
ይሁን እንጅ የአውሮፓ ህብረት ለድርጅቱ የሰጠውን የባለቤትነት ዕውቅና እስካሁን ድረስ አላነሳም።
ምንጭ፦ www.dw.com/en