ደንበኞች ለሞከሩት ወይም ለለኩት ልብስ ገንዘብ የሚያስከፍለው ሱቅ
አዲስ አበባ ፣ ጥር 13 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በስፔን የሚገኝና የተዘጋጁ የወንድ ሙሉ ልብሶችን ጨምሮ ውድ ጫማዎችና መዋቢያዎችን የሚሸጠው ሱቅ ደንበኞቹን የሚያስተናግድበት መንገድ አነጋጋሪ ሆኗል።
በቢልባኦ ከተማ የሚገኘውና ፓስኳል ቢልባኦ የሚል ስያሜ ያለው ይህ ሱቅ ደንበኞቹ ከገቡ በኋላ ግብይት ፈጸሙም አልፈጸሙ በግብር መልክ ማስከፈል መጀመሩ ተገልጿል።
ሸማቾች ወደ ሱቁ ጎራ ካሉ መግዛት አልያም ደግሞ አለመሞከር ግድ ይላቸዋል፤ ወደ ውስጥ ከገቡ በኋላ ልብስ፣ ጫማ አልያም ሌሎች እቃዎችን ከሞከሩ ወይም ከለኩ ይህን ላደረጉበት ክፍያ ይጠየቃሉና።
የሱቁ ህግ ሳይገዙ ሞክረው የሚወጡ ሸማቾች 15 ዩሮ መክፈል ይጠበቅባቸዋል ይላል።
አዲሱ አሰራር ደግሞ ሱቁ ደንበኞቹን እንደ መለኪያ ይጠቀምበታል ነው የተባለው።
የሱቁ ባለቤት ካሚኖ አዙላ ፓስኳል ብዙ ሰዎች ከወዳጆቻቸው ጋር ወደ ሱቅ ጎራ ካሉ በኋላ በሚፈልጓቸው ሸቀጦች ላይ አስተያየትና ምክር ከጠየቁ በኋላ ወደ ሌሎች ቦታዎች በመሄድ በርካሽ ዋጋ እንደሚገዙ ይናገራሉ፤ በዚህም የእኛ ጊዜ ይባክናል ባይ ናቸው።
ይህ ደግሞ መግዛት ከማይፈልጉ ሰዎች ጋር ጊዜን ማባከን ተቀባይነት የሌለው በመሆኑ፥ ከዚህ ዓመት ጀምሮ የሱቁን ሸቀጦች በማየት በሚሞክሩ ሰዎች ላይ የ15 ዩሮ ግብር ተግባራዊ አድርገናል ብለዋል።
ይህም ቢያንስ ወደ ሱቁ የመጣው ገዥ በቀረበው ምርት እና ዋጋ ላይ ያለውን ፍላጎት ለማወቅ እንደሚረዳም ገልጸዋል።
ከሱቁ አሰራር ጋር ተያይዞ ከተጠቃሚዎች የቀረበ ቅሬታ ስለመኖር አለመኖሩ ግን የተባለ ነገር የለም።
ምንጭ፦ ኦዲቲ ሴንትራል