Fana: At a Speed of Life!

በምርጫው ሂደት የሳይበር ጥቃት እንዳያጋጥም በልዩ ትኩረት እየሰራን ነው -ኤጀንሲው

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 27 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በምርጫው ሂደት የሳይበር ጥቃት እንዳያጋጥም በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ገለጸ።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሹመቴ ግዛው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫውን ከሚያስፈጽምባቸው ግብአቶች አንዱ የሚጠቀምባቸው ቴክኖሎጂዎችና የአሰራር ሥርዓቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።
በመሆኑም የምርጫ ባለድርሻ አካላት የሳይበር ምህዳር አጠቃቀማቸው ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው ብለዋል።
በምርጫ ሂደቱ ቴክኖሎጂዎችና አሰራሮቹ ለሳይበር ጥቃት እንዳይጋለጡ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ድጋፍና ክትትል እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ለሳይበር ጥቃት ቢጋለጡና ሀገርና ህዝብን በእጂጉ ሊጎዱ የሚችሉ ተቋማትን በመለየት ኤጀንሲው በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑን ነው የተናገሩት።
ከነዚህ ተቋማት አንዱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ምርጫ ቦርድ መሆኑን ገልፀው ዕጩ ተወዳዳሪዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ከምርጫው ጋር በቀጥታም ሆነ በተዛዋዋሪ የሚገናኙ ተቋማት የሳይበር ጥቃት ኢላማ ሊሆኑ ስለሚችሉ እንዲጠነቀቁ መክረዋል።
መረጃ ሰርሳሪዎች ሐሰተኛ መረጃዎችን በማሰራጨትና መረጃ የማዛባት፤ መረጃን የማመሰቃቀል ተግባር ሊያከናውኑ እንደሚችሉም መጠቆማቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የምርጫ ባለድርሻ አካላቱ ‘’የሳይበር ጥቃት ደርሶብናል’’ በሚሉበት ወቅት ኤጀንሲው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ዶክተር ሹመቴ አረጋግጠዋል።
ኤጀንሲው ቁልፍ በሆኑ አገራዊ መሰረተ ልማቶች ላይ ጥቃት እንዳይደርስ የሚከላከል ቡድን ማቋቋሙን ጠቅሰዋል።
ቡድኑ በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫ ወቅትና በድህረ ምርጫ ወቅቶች ሊያጋጥሙ የሚችሉ የሳይበር ጥቃቶችን ለመከላከል ዝግጁ መሆኑንም ገልጸዋል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.