የደቡብ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት በመደበኛ ስብሰባው በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ በመምከር ውሳኔ አሳለፈ
አዲስ አበባ፣ ጥር 12፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የደቡብ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት ባካሄደው 209ኛ መደበኛ ስብሰባው በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ በመምከር ውሳኔ አሳለፈ።
መስተዳድር ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ የማዕድን ስራዎች ረቂቅ ደንብ ላይ በዝርዝር በመወያየት ውሳኔ ማሳለፉን ከክልሉ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በተለይ በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች ልዩልዩ ማዕድናት የሚመረቱ ቢሆንም ከማዕድን ምርቶቹ ህብረተሰቡ ተገቢውን ጥቅም እያገኘ አለመሆኑን ምክር ቤቱ ገምግሟል።
መስተዳድር ምክር ቤቱ የማዕድን ስራዎች ረቂቅ ደንብ ላይ በመወያየት የባህላዊ፣ የልዩ አነስተኛና የአነስተኛ ደረጃ ማዕድን ማምረት ስራ ፈቃድ አሰጣጥ፣ የሮያሊቲ፣ የመሬት ኪራይና የገቢ ግብር ክፍያዎችን መጠንና የአከፋፈል ሁኔታዎችን በዝርዝር በመመልከት የቀረበውን ደንብ አጽድቋል።
መስተዳድር ምክር ቤቱ የከተማ ቀበሌ አደረጃጀት አስመልክቶ በቀረበ የውሳኔ ሀሳብ ላይ በመወያየትም አጽድቆታል።
በክልሉ የሚገኙ ከተሞች የቀበሌ ምክር ቤቶች እና ይህንን መሰረት አድርጎ ስለሚደራጀው የከተማ ምክር ቤት መስተዳድር ምክር ቤቱ በዝርዝር መክሮ ውሳኔ አሳልፏል።
በከተሞች ነዋሪውን ህብረተሰብ በልማት ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ እና ያልተማከለ አስተዳደርን በመተግበር በነቃ ህዝባዊ ተሳትፎ ቀጣይነት ያለው ልማት ለማረጋገጥ እንዲቻል የክልሉን ከተሞችና የከተማ ቀበሌያትን በአዲስ መልክ በማዋቀር በየደረጃው ምክር ቤቶችን ማደራጀት እንደሚያስፈልግም መስተዳድር ምክር ቤቱ በዝርዝር ከተመለከተ በኋላ ውሳኔ አሳልፏል።
መስተዳድር ምክር ቤቱ የክልሉን መንግስት አስፈጻሚ አካላት አደረጃጀትና አሰራር መመሪያ የተመለከተ ሲሆን የክልሉን አስፈጻሚ መስሪያ ቤቶች በዘርፍ በማደራጀት ውጤታማነታቸውን እየገመገመ ለመምራት እንዲያስችል የቀረበውን መመሪያ መርምሮ አጽድቋል።