Fana: At a Speed of Life!

ለጸጥታው ምክር ቤት አባል ሃገራት አምባሳደሮችና ለደቡብ አሜሪካ ሃገራት በወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ ገለጻ ተደረገ

አበባ፣ ሚያዝያ 28፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ለመንግስታቱ ድርጅት የሰላምና ጸጥታው ምክር ቤት አባል ሃገራት አምባሳደሮችና ተቀማጭነታቸው በአዲስ አበባ ከተማ ላደረጉ የደቡብ አሜሪካ ሀገራት አምባሳደሮች በወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ ገለጻ አደረጉ፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው በትግራይ ክልል፣ በኢትዮ-ሱዳን ድንበር፣ በህዳሴ ግድቡ እና በመጪው ምርጫ ዙሪያ ነው ለአምባሳደሮቹ ማብራሪያውን የሰጡት፡፡

በትግራይ ክልል እስካሁን መንግስት 70 በመቶ የሚደርሰውን የሰብዓዊ ድጋፍ እያቀረበ መሆኑን የጠቀሱት አምባሰደሩ ዓለምአቀፉ ማህበረሰብ ድጋፉን እንዲያጠናክር አሳስበዋል፡፡

ሱዳን በትግራይ ክልል የተካሄደውን የህግ ማስከበር ተከትላ የኢትዮጵያን ድንበር መውረሯን ገልጸዋል፡፡

እንዲሁም ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ላይ የይገባኛል ጥያቄ ማንሳቷ ፍጹም ተገቢነት የሌለው ነው ያሉት ሚኒስቴር ዴኤታው ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሱዳን ላይ ጫና እንዲፈጥር ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በህዳሴ ግድቡ ዙሪያም ሱዳን ያነሳቻቸው ጥያቄዎች ምላሽ ማግኘቷን አንስተው በግብጽ በኩልም በቅርቡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ግድቡ በሀገራቸው ላይ ጉልህ ተጽዕኖ እንዳማይፈጥር መናገራቸውን አስታውሰዋል፡፡

በመጪው ምርጫ ዙሪያ ማብራሪያ የሰጡት ሚኒስትር ዴኤታው ከ34 ሚሊየን በላይ ሰው ለመምረጥ መመዝገቡንም ገልጸዋል፡፡

የአውሮፓ ህብረት የምርጫ ታዛቢዎችን ላለመላክ መወሰኑ ቅሬታ እንደሚፈጥር አንስተው ህብረቱ ውሳኔውን ዳግም እንደሚያጤነው ተስፋቸውን ገልጸዋል፡፡

ማብራሪያ የተሰጣቸው አምባሳደሮች በበኩላቸው በትግራይ ክልል እየተካሄደ ስለሚገኘው የሰብዓዊ ድጋፍና በክልሉ በቀላሉ ለመንቀሳቀስ የሚያስችል አሰራር በመዘርጋቱ እና ከቪዛ ስርዓት ጋር በተገናኙ ጉዳዮች ዙሪያ ገለጻ ስለተደረገላቸው ምስጋና ማቅረባቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.