በአጣዬና አካባቢው ለደረሰው አደጋ 144 ሚሊየን ብር የሚገመት ድጋፍ ተደረገ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 21፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የገቢዎች ሚኒስቴር እና የጉምሩክ ኮሚሽን በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በአጣዬና አካባቢው ለደረሰው አደጋ 144 ሚሊየን ብር የሚገመት ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡
ድጋፉ በኮንትሮባንድ መከላከል ስራ የህይወት መስዋዕትነት ተከፍሎባቸው የተያዙ ምግብ ነክ ቁሳቁሶችና አልባሳት ናቸው ተብሏል፡፡
ጉዳት የደረሰባቸው አካባቢዎች የሚመለከታቸው የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት በዛሬው ዕለት የድጋፍ ርክክብ ተደርጓል፡፡
ድጋፍ በተደረገበት ወቅት የገቢዎች ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ ላቀ አያሌው በአጣዬና አካባቢው በደረሰው የሰው ህይወት መጥፋትና የንብረት ውድመት የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸዋል፡፡
ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ሁሉም ዜጋ ህግና ስርዓት እንዲከበር መስራት እንዳለበትና ከጅምላ ማወደስና ከጅምላ ፍረጃ በመውጣት ሁሉም የተጣለበትን ኃላፊነት ሊወጣ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
አክለውም የህይወት መስዕዋትነት ተከፍሎ በቁጥጥር ስር የዋሉ የህዝብ ሀብቶች ለህዝብ እንዲውል የተደረገ መሆኑን ገልፀው ዕቃዎቹን በመያዝ ኃላፊነታቸውን የተወጡ የጉምሩክ አመራሮችና ሰራተኞች እንዲሁም የጸጥታ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ በበኩላቸው ኮንትሮባንዲስቶችና ህገ-ወጦች በሀገራችን ላይ የደቀኑትን አደጋ ለመቀልበስ በተለይም የህገ-ወጥ መሳሪያ እና አደንዛዥ ዕፅ ዝውውር ከሚችሉት አደጋ አንፃር መከላከል የተቻለው የሚደንቅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ኮሚሽኑ መደበኛ ስራዎችን በኋላፊነት መስራት እንደተጠበቀ ሆኖ በሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋ የተጎዱትን መደገፍ አፅንኦት ሰጥተን የምንሰራው ነው ብለዋል፡፡
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክጸር ፋንታ ማንደፍሮ የገቢዎች ሚኒስቴር እና የጉምሩክ ኮሚሽን በተለያየ ጊዜ በአማራ ክልል በሚፈጠሩ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት ለተጎዱ አካላት ድጋፍ በማድረግ ተምሳሌት መሆኑን አንስተው ሌሎች ተቋማትም በዚህ መልኩ በተለይ ጉዳት የደረሰባቸውን ከተሞች መልሶ በማቋቋም ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ድጋፉን የተረከቡት የአማራ ክልል የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ቢሮ ኃላፊ አቶ ዘላለም ልጅአለም፣ የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና መመሪያ ኃላፊ አቶ መሐመድ ኢማም እና የሰሜን ሸዋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ታዬ የድጋፍ ቁሳቁሶቹ በፍጥነት ለተጎጂዎች እንደሚያደርሱ በመግለፅ የተፈናቀሉትን ወደ ቤታቸው ለመመለስ እና መልሶ ለማቋቋም የተጠናከረ ድጋፍ እንዲደረግ መጠየቃቸውን ከገቢዎች ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!